ኢሰመኮ ይፋ ባደረገው ሪፖርት በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ ያላቸውን ጉዳዮች የዘረዘረበት ክፍል ከዚህ የሚከተለውን አስፍሯል። ሪፖርቱ ቀን፣ ቦታና ስም በመጥቀስ የተፈጸሙ ወንጀሎችን፣ ግድያዎችን፣ ዘረፋና የመሳሰሉትን በዝርዝር አስቀምጧል። ሙሉ በሙሉ እንዳለ ከሪፖርቱ የተቀዳ ነው። ከቀረበው የፒዲኤፍ ሪፖርት ላይ የተወሰደው መረጃ እንዳለ ቀርቧል።
- በኦሮሚያ ክልል በዋነኛነት በመንግሥትና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ” ኦነግ ሽኔ ” መካከል በሚደረገው የትጥቅ ግጭት ዓውድ ውስጥ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ በምሥራቅ ሸዋ ዞን፣ ምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ፥ አርሲ እና በሌሎች ዞኖች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች አሳሳቢነታቸው ቀጥሏል፡፡
- ሐምሌ 26/2016 ከአማራ ክልል ባሕርዳር ከተማ ወደ አዲስ አበባ 66 ተሳፋሪዎችን የያዘ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ በፊቼ እና ገበረ ጉረቻ መሃል ሲደርስ ” ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን እገታ ተፈጽሞ 2 ሰዎች ተገድለዋል፤ ቀሪዎቹን አግቶ የወሰደ ሲሆን ለእያንዳንዱ ታጋች መለቀቂያ እስከ 1 ሚሊየን ብር መክፈል እንዳለባቸው ለቤተሰባቸው በማሳሰብ ደጋግመው እየደወሉ ክፍያው በቶሎ ካልተፈጸመ ግድያ እንደሚፈጽሙባቸው ሲያስፈራሩ እንደነበር በወቅቱ ከታጋች ቤተሰቦች ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
- ነሐሴ 3/2016 ዓ.ም. በግምት ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት አካባቢ በኦሮሚያ ክልል፣ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን፣ አቤ ዶንጎሮ ወረዳ፣ ጨሩ ቀበሌ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የተገለጸ በተለምዶ ” ፋኖ ” ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ 22 ሰዎች ተገድለዋል በ4 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፤ 540 መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል እንዲሁም በግምት 800 አካባቢ ከብቶች በታጣቂ ቡድኑ ተወስደዋል።
- ነሐሴ 7/2016 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል፤ አርሲ ዞን፣ አስኮ ወረዳ፤ ጠለፋ ጨፋ ቀበሌ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት / ኦነግ ሽኔ ታጣቂዎች ወደ ቀበሌው ገብተው የቀበሌው አስተዳደር ሲቪል ሠራተኞች እና ከመንግሥት ጋ ርግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠቆሙ ነዋሪዎችን ለይተው በፈጸሙት ጥቃት 3 ሰዎችን ገድለዋል።
- ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ሰሜን ሽዋ ዞን፣ አቦቴ ወረዳ፣ ኤጄሬ ከተማ ነዋሪ የሆነ 1 ሰው በመንግሥት ኃይሎች ተገድሏል፡፡
- ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኙት አመያ፣ ቀርሳ ማሊማ፣ ሰደን ሶዶ እና ቶሌ ወረዳዎች ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት / ኦነግ ሸኔ / ታጣቂዎች በሐምሌ እና በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም. ብቻ 14 ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያ ስለመፈጸሙ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
- ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም. ምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ ጊዳ አያና ወረዳ አንዶዴ ዲቾ ቀበሌ የ03 ቀበሌ በአካባቢው እንደሚንቀሳቀስ የተገለጸ ” ፋኖ ” ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ በተፈጸመባቸው ጥቃት 3 ሰዎች ተገድለዋል::
- መስከረም 25/2017 ዓ.ም. ቄለም ወለጋ ዞን፣ ሳጃ ወለል ወረዳ፣ የላሎ ገለታ ቀበሌ ነዋሪ 2 ሰዎች በመንግሥት ኃይሎች ተገድለዋል፡፡
- መስከረም 28/2017 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን፣ አመያ ወረዳ ኢተያ ገምባ ጀቴ፣ ኢላላ እና ጢሮ ኢላላ ቀበሌዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት / ኦነግ ሽኔ ታጣቂዎች 5 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል፡፡
- መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ምዕራብ ሽዋ ዞን፤ አመያ ኢተያ ገምባ ጀቴ ቀበሌ የመንግሥት ኃይሎች 9 ሰዎችን ገድለዋል፡፡
- ጥቅምት 9 ቀን 2017 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ቤጊ ወረዳ፤ የኮበሬ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ 1 ሰው ለኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት / ኦነግ ሸኔ “ድጋፍ አድርገሃል” በሚል በመንግሥት ኃይሎች ተገድሏል፡፡
- ጥቅምት 12/2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ ቆንዳላ ወረዳ፣ የወንዲ ዶች ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ 1 ሰው ” ለኦሮሞ ነጻነት ስራዊት/ኦነግ ሸኔ ድጋፍ አድርገሃል” በሚል በመንግሥት ኃይሎች ተገድሏል፡፡
- ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. በምሥራቅ ሽዋ ዞን፣ ዱግዳ ወረዳ፣ ብርቢሣ እና ጋሌ በተባሉ ቀበሌዎች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት/ኦነግ ሸኔ አባላት 38 ሲቪል ሰዎችን ገድለዋል።
- ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም. በምሥራቅ ሽዋ ዞን፣ ዱግዳ ወረዳ፣ መጃ ላሉ ቀበሌ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት/ኦነግ ሽኔ አባላት በቀበሌው የሚኖሩ 12 ስዎችን ገድለዋል፡፡
- ኅዳር 19/2017 ዓ.ም. የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት/ኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በአርሲ ዞን፣ ሽርካ ወረዳ፣ ሶሌሳ ረከታ እና መከና ቀበሌዎች በፈጸሙት ጥቃት 13 ሰዎችን ገድለዋል፡፡
- የካቲት 5/2017 ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት በጅማ ዞን ጌራ ወረዳ ዋላ ቀበሌ ቦሬ ከተማ አቶ ዛኪር አባኦሊ የተባሉ ሰው በመኖሪያ ቤታቸው እያሉ ማንነታቸው ባልታወቀ ግለሰቦች በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ይህንን ተከትሎ በተከሰተው ግጭት የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም. 293 መኖሪያ ቤቶች፣ 11 የእህል ወፍጮዎችና 7 ትራክተሮች ተቃጥለዋል፡፡ ከቃጠሎ የተረፉ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ የምግብ እህሎች እና የቀንድ ከብቶችም የተዘረፉ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ የአማራ ብሔር ተወላጆች ወደ አጎራባች አካባቢዎች ተፈናቅለዋል፡፡
- መጋቢት 8/2017 ዓ.ም. በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው የታጠቀ ቡድን (የፋኖ አባላት) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሽዋ ዞን ግንደበረት ወረዳ ጭረቻ ገቶ ቀበሌ በመግባት በ2 ሰዎች ላይ ግድያ ፈጽመዋል፡፡
- ሚያዝያ 1 ቀን 2017 ዓ.ም. የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት / ኦነግ ሽኔ ወደ ሀሮ ወረዳ ሱጌ ቀበሌ በመግባት 10 ሰዎችን ገድለዋል፡፡ በተመሳሳይ ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም. የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት/ኦነግ ሽኔ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ቀበሌው ዘልቆ በመግባት 3 ሰዎችን ገድለዋል፡፡
- ማንነታቸውን በውል ማወቅ ያልተቻለ የታጠቁ ኃይሎች ግንቦት 1/2017 ዓ.ም. በሰሜን ሽዋ ዞን ወረ ጃርሶ ወረዳ፣ ከወረዳ ዋና ከተማ ጎሀጽዎን ልዩ ስሙ አገምሳ ተብሎ በሚታወቅ ቦታ ወደ ንጋት አካባቢ ወደ ነዋሪዎች ቤት ላይ በመተኮስ ከ8 ሰዎች በላይ ገድለዋል።
- ግንቦት 9/2017 ዓ.ም. በኢሉባቦር ዞን ዳሪሙ ወረዳ ቤና ቶኮፋ እና ቤና ለመፋ በሚባሉ ቀበሌዎች የመንግሥት ኃይሎች 7 ሰዎችን ገድለዋል።



