የአማራ ክልል የልማት ድርጅቶች ከሚባሉት መካከል አንዱ የሆነው የጸደይ ባንክ በዓመቱ መጨረሻ 870 ሚሊዮን ብር ከስሯል። የኢትዮሪቪው ተባባሪ ከባህር ዳርና አካባቢው ባሰባሰበው መረጃ ባንኩን ያከሰረው ዝርፊያ ነው። በባንኩ ቅርንጫፎች ገንዘብ ሲኖር ዘራፊዎች መረጃ እንዲደርሳቸው ይደረጋል።
ስማቸውን ለመግለጽ የሚፈሩና በሚፈጸመው ነወር ተግባር ማዘናቸውን የገለጹ እንዳሉት የጸደይ ባንክ በፍጹም ሊከስር አይችልም። ባንኩ የክልሉ ሃብት በመሆኑ በክልሉ በስፋት እስከ ገጠር ድረስ የተዘረጋ፣ የየአካባቢው የክልሉ መንግስት የአስተዳደር መዋቅር ድጋፍ የሚያደርግለት ተቋም ስለሆነ ኪሳራ ከቶውን የሚታሰብ እንዳልሆነ እነዚሁ ወገኖች ያስረዳሉ።
ለሃያ ስድስት ዓመታት የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም በሚል ስያሜ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ተቋም ፀደይ ባንክ ተብሎ ወደ ባንክነት አድጎ ስራ የጀመረው በመስከረም 2015 ነበር።

በባንኩ ይፋዊ ስራ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት ዶክተር ይልቃል ከፋለ ፣የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይና የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ተገኝተው እንደነበር በወቅቱ መዘገቡ አይዘነጋም።
ከአገር እስኪወጡና በይፋ የፋኖ ትግልን መቀላቀላቸውን እስካሳወቁ ድረስ የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ነበሩ። በማስጀመሪያው ስነ ስርዓ ላይ ይፋ እንደሆነው በ2015 ባንኩ አስራ ሁለት ሚሊዮን ደንበኞችና 500 ቅርንጫፎች ነበሩት።
አሁን ላይ ደግሞ ፀደይ ባንክ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ሃብት፣ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ካፒታል እና ከ9 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ያለው ግዙፍ ባንክ እንደሆነ በባንኩ ድረገጽ ላይ እ እ አ በኦክቶበር 2024 ፕሬዚዳንቱን አቶ መኮንን የለውምወሰን ጥቅሶ ጽፏል። ከ627 በላይ በሚሆኑ ቅርንጫፎቹም በመላ ሃገሪቱ ከ14 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የቁጠባ እና ከ1 ሚሊዮን በላይ የብድር ደንበኞችን እያገለገለ እንደሚገኝም አብሮ ተመልክቷል።
መረጃ ያጋሩን እንደሚሉት በዚህ ደረጃ ያለ ባንክ በፍጹም ሊከስር እንደማይችል ነው። ከደንበኞች አገልግሎት ባለፈ ለሌሎች ባንኮች ብር የሚያበድረው ጽደይ ባንክ፣ ብድር ለመስጠት፣ የሰጠውን ብድር ለመሰብሰብ ችግር እንደሌለበትም እነዚሁ ምንጮች ይገልጻሉ። ጥያቄያቸው የመንግስት መዋቅሮች በሙሉ ያበደረውን የሚሰበስቡለት፣ ወይ እንዲሰበስብ ድጋፍ የሚያደርጉለት ባንክ የከሰረው ከውስጥ መረጃ የሚያቀብል በመኖራቸው እንደሆነ ይገልጻሉ።
ዛሬ ላይ የቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የቀድሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳስደር ከንቲባና አሁን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሀላፊ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ መሆናቸውን የሚጠቁሙት እነዚህ ክፍሎች እሳቸውም ሆኑ የባንኩ የበላይ ኃላፊዎች ለኪሳራው ሊሰጡ የሚችሉት በአመክንዮ የሚደገፍ ምክንያት እንደማይኖራቸው ገልጸው ባንኩ በዝርፊያ የሕዝብ ሃብት እንዳጣ ይገልጻሉ።
በአማራ ክልል ሁለት ቦታ የሚጫወቱ እንዳሉ በስፋት ይገለጻል። መከላከያ እርምጃ ሊወስድ ሲል ሳይቀር አስቀድመው መረጃ የሚያሾልኩ መኖራቸውን ሕዝብ አደባባይ የሚመሰከረው ጉዳይ እንደሆነ ተባባሪያችን ከላከው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል።
እገታ፣ አፈናና ዝርፊያ እጅግ በተስፋፋበት ወቅት መዋቅር ውስጥ የዘለቀ እርምጃ ሲወሰድ ችግሩ ተቃሎ እንደነበር የሚናገሩ የባህር ዳር ነዋሪዎች፣ አንድ ባለስልጣን ከዚሁ ወንጀል ጋር በተያያዘ በጸጥታ ኃይሎች ሲያዙ ወደ አዲስ አበባ አንድ ክልሉ ላይ ተጽዕኖ ለሚፈጥሩ ከፍተኛ ባለስልጣን ወዲያው በመደወል እንዲለቀቅ መደረጉንና ይኸው ሰው አሁን ድረስ በኃላፊነቱ ላይ እንደሚገኝ ስም ጠርተው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ከጸደይ ባንክ መረጃ ያላቸው እንደሚሉት ባንኩ በዝርፊያ ለኪሳራ የተዳረገው የትኞቹ ባንኮች ላይ ገንዘብ እንዳለ አስቀድሞ ለታጣቂዎች መረጃ በውመስጠት ነው። መረጃ የሚደርሳቸው ታጣቂዎች ባንኩን በተደጋጋሚ እንደዘረፉት የሚያመለክቱ ምንጮች ዘረፋው የተለመደ መሆኑን ያመለክታሉ። በዜናም እንደሚዘገብ ይገልጻሉ።
በጸደይ ባንክ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በነጻ አውጪነትና በትግል ስም መሳሪያ አንግበው በሚዲያ ድጋፍ የሚደረግላቸው አብዛኞቹ “ስራ” እያሉ የሚጠሩት በዝርፊያ የመክበር ጉዳይ ነው። ከተለያዩ አካባቢዎች የሚሰሙ አቤቱታዎች እንደሚመሰክሩት ጫካ ሆነው ሃብት ያከማቹ ጥቂት አይደሉም።
መዋቅር ውስጥ ካሉ ኃላፊዎች ጋር በመቀናጀት እንደሚፈጸም የሚነገርለት ይህ ሕዝብን ግራ ያጋባ ዘረፋ የሚጠራበት አጋባብ ካልተፈጠረ ወደፊት ችግሩ ሰፊ አገራዊ መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል ጉዳዩ ያሳሰባቸው ደጋግመው ሲወተውቱ እየተደመጠ ነው። ራሱ ገዢው ፓርቲ በሁለት ካባ መጫወት እንደማይቻል ባስታወቀበት የሰሞኑ መግለጫው ውስጡን እንደሚያጠራ ሲያስታውቅ ችግሩን አምኖ ነበር።

