የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጉን ካስታወቀ በሁዋላ የተደረገውን የምንዛሬ ተመን ተከትሎ የትይዩ ምንዛሬው ወይም የጥቁር ገበያው ዋጋ መናር ሰፊ መነጋገሪያ ከሆነ ሰነባብቷል። በተለይም ባንኩ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለባንኮች እያቀረበ ባለበት ወቅት የጥቁር ገበያው መጨመር ነበር እንቆቅልሹ።
ይህን መነጋገሪያ አጀንዳ ተከትሎ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወሰድ ይፋ መሆኑን ተከትሎ፣ በሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ የወንጀል ተግባር ላይ የተሰማሩ 138 ተጠርጣሪዎች የባንክ ሂሳብ መታገዱን የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል።
አገልግሎቱ ይፋ ባያደርገውም እገዱ ውስጥ ተቀማጭነታቸው ውጭ አገር የሆነና በአገር ቤት አስመጪና ላኪ ድርጅት ያላቸው ወይም በሽርክና የሚሰሩትን እንደሚያካትት ኢትዮሪቪው መረጃ አላት። እነዚህ አካላት ከውጭም ከውስጥም ዶላር እየለቀሙ ለሌሎች አካላት እንደሚያሻግሩ በተደጋጋሚ ስም እየጠቀሱ ጥቆማ የሚሰጡ ጥቂት አይደሉም።
ቀደም ሲል ወይዘሮ ፈትለወርቅ ሞንጆሪኖ ሲመሩት የነበረው የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የ138 ተጠርጣሪዎችን የባክን ሂሳብ ከማገዱ በፊት፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ፣ ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ የመደበኛ ባንክ ሥርዓት በማይጠቀሙ አካላት ላይ እስከ መውረስ የሚደርስ ርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቀቀው ነበር።
የባንክይ ገዢ አክለውም መቀመጫቸውን ውጭ ሀገራት አድርገው በህገ ወጥ ገንዘብ ማስተላለፍ ላይ በመሰማራት የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት ታማኝነት ለመሸርሸርና የገበያ ዋጋን ለማዛባት በሚሰሩ ወንጀለኞች ላይ የሚወሰደው ርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀው ነበር።
ባንኩም ባወጣው መግለጫ የአራት ህገወጥ ምንዛሬ ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችንና ስማቸውን ያልገለጻቸውን በዱባይ የሚገኙትን ጠቅሶ ሕገወጦችን አስታውቆ ነበር።
የፋይናንስ አገልግሎቱ ባሰራጨው መግለጫ ሕጋዊና መደበኛ የባንክ ስርዓትን ወደ ጎን በመተው በህገ-ወጥ እና ትይዩ ገበያ የውጭ ምንዛሪ ወንጀል ላይ የተሰማሩ 138 ዋነኛ ተጠርጣሪዎች የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲታገድ ማድረጉን ያስታወቀው በየደረጃው መረጃዎች ይፋ ከሆኑ በሁዋላ ነው።
የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት በሕጋዊና መደበኛ የባንክ ሥርዓት በኩል እንዲከናወን በግልጽ የተቀመጠ መሆኑን ያወሳው መግለጫው፤ በሕገ-ወጥ መንገድ የምንዛሪ አገልግሎት ላይ የተሰማሩት ላይ ጠንካራ የሕግ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በወንጀል ድርጊቱ ላይ ተሰማርቶ መገኘት የንብረት መወረስን ጨምሮ በከፍተኛ ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ በመሆኑ የንግዱ ማህበረሰብ መደበኛ የባንክ ስርዓትን እንዲጠቀም በመንግስት በኩል ማሳሳቢያ ሲሰጥ ቆይቷል ብሏል።
ሆኖም ግን አንዳንድ የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ ወንጀልን እንደ መደበኛ የንግድ ስራ በመያዝ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በመሆናቸው ክትትል ሲደረግባቸው ቆይቷል ሲል ገልጿል።
በዚሁ መሠረት ክትትል ተርጎ የተደረሰባቸው እና በህገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ ላይ የተሰማሩ 138 ዋነኛ ተጠርጣሪዎች የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲታገድ ተደርጓል፡፡
ብሄራዊ ባንክ የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት መደበኛ የባንክ ስርዓትን የማይጠቀሙ ግለሰቦችንም ሆነ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀመር ከቀናት በፊት ማሳወቁ ይታወሳል።

