በዋጋ ግሽበት ድሃው ማህበረሰብ እንዳይሰቃይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ በተለይም የግብርና ስራዎች ላይ በስፋት እንዲሰራ የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤት እና ሊቀመንበር ሼይኸ መሀመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ አሳሰቡ።
“በግብርናው ዘርፍ በሰፊው ስሩ” ሲሉ ማሳሰቢያና አደራ ያስተላለፉት ሼይኸ መሀመድ፣ ይህ ሲሆን የኢትዮጵያ ህዝብም እንደሚጠቀም ገልጸዋል። አክለውም “አሁንም ወደፊትም ምኞቴ ይሄ ነው” በማለት “እኮራባችኋለሁ፣ እወዳችኋለሁ” ላሉዋቸው የሚድሮክ ግሩፕ አመራሮችና ሰራተኞች አደራቸውን አጽንተዋል።
ሼይኸ መሀመድ ይህን ያሉት ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በ2017 ዓ.ም ያከናወናቸውን ተግባራት እና ያጋጠሙትን ችግሮች አስመለክቶ አጠቃላይ ዓመታዊ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ባከበረው ዓመታዊው የቤተሰብ ቀን ባቀረበበት ወቅት ካሉበት ሳዑዲ በቪዲዮ የቀጥታ መልዕክት ነው።
በንግግራቸው መጀመሪያ ” የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አልቆ በመመረቁ እኛም ለልማታችን ስለምንፈልገው ደስ ብሎኛል፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብም እንኳን ደስ አላችሁ ” ሲሉ ስሜታቸውን አድምቀው አስተላልፈዋል። ባለሃብቱ ለሕዳሴ ግድብ በድርጅቶቻቸውና በራሳቸው ስም ከፍተኛ ሃብት መደጎማቸው አይዘነጋም።
ሼይኸ መሀመድ አክለውም ሚድሮክ ባለፉት አምስት ዓመታት ያሳየውን ትጋት አድንቀዋል። በዚህም ትጋትና ልፋት የሚያኮራ ውጤት መመዘገቡን እንደተረዱና እንደሰሙ አመስግነዋል። ኩራት እንደሚሰማቸውም አመልክተዋል። አያይዘውም ከቀድሞው በበለጠ የሚድሮክ ሰራተኞች ቁጥር እንዲጨምር እንደሚፈልጉም አስታወቀዋል።
አቶ ጀማል መሐመድ ሚድሮክ ራሱን አይቶና ማስተካከያ እርምጃዎች ወስዶ ወደ ተግባራ ባይገባ ኖሮ የመፍረስ አደጋ ላይ ደርሶ እንደነበር ካወሱ በሁዋላ የተደረገው ማሻሻያና ሰራተኞች በአዲስ መንፈስ አንድ ሆነው በመስራታቸው ይህ ውጤት እንደተመዘገበ አመልክተዋል።
አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑን ያስታወቁት ሼይኸ መሀመድ፣ በዚህም የተነሳ የሰራተኞች ቁጥር እንደሚጨምር አስታውቀዋል። “ምኞቴ” አሉ ሼይኸ መሀመድ አክለው ፣ “ምኞቴ ኢትዮጵያ ውስጥ የመካከለኛ ገቢ ማህበረሰብ ተፈጥሮ ማየት ነው” ብለዋል። “በሚድሮክ ላይ ተሳተፉ መልካም ነው፣ እኛም ሀገሪቱንም እንጠቅማለን ” ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላለፈዋል።
“አሁን የተገኘው ውጤት በሰራተኞች እና በስራ ሃላፊዎች ልፋት ነው፣ አሁንም በርቱ ። በተገኘው ውጤት ደስ ብሎኛል አመሰግናለሁ ” ሲሉ ሼይኸ መሀመድ አድናቆታቸውንም ገልጸዋል።
” የሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ሰፊ እና ታላቅ ናቸው። አመራሮች ታውቁታላችሁ ዝርዝር አያስፈልግም፣ ሚድሮክ ይዞት የነበረው ዓላማ ይህ ብቻ አይደለም ይቀጥላል ” ሲሉ ሼይኸ መሀመድ መልዕክታቸውን አሳርገዋል።
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በ2017 ዓ.ም ያከናወናቸውን ተግባራት እና ገጥመውት የነበሩ ችግሮችን የሚያሳይ አጠቃላይ አመታዊ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ዓመታዊውን የቤተሰብ ቀን ሲያከብር አቅርቧል።
ሪፖርቱን ያቀረቡት የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የእቅድና ሪፖርት ኮርፖሬት ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉት የጸጥታ ችግሮች በስራቸው ላይ ጫና አሳድረውባቸው እንደነበር ገልጸዋል። የብድር አገልግሎት ማግኘት የማይቻልበት ደረጃ ተደርሶ ነበር። ብድር ሲገኝም የወለድ ምጣኔያቸው ከፍ ማለት ተጽዕኖው ከፍተኛ እንደነበር አስታወቀዋል።
በስነ ስርዓቱ ላይ 588 ለሚሆኑ ግንባር ቀደም ሰራተኞቹ ከ100ሺ እስከ 500ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት እና እውቅና ሰጥቷል።
” በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የደሴ፣ የነቀምት፣ የአሶሳና የሰመራ የዱቄት ፋብሪካዎች ግንባታ ተጠናቆ ተመርቋል። ለ6ሺህ ሰዎች በአራት የምገባ ማዕከላት በሚደረግ ድጋፍ ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ አድርገናል።
በማኑፋክቸሪንግ፣ ማይኒንግ እና በሆቴልና ሪዞርት ዘርፎች ከእቅድ ከፍ ያለ የሽያጭ አፈጻጸም ታይቷል፡፡ በተጨማሪም ሁሉም ዘርፎች አትራፊ ሆነዋል። ከአግሮ፣ ኮሜርስ፣ ከኮንስትራክሽን እና ሪል እስቴት በቀር ሁሉም ካቀዱት በላይ ትርፍ አስመዝግበዋል።
ከድርጅቶቻችን ሽያጭና ትርፍ አፈፃፀም ሆራይዘን ፕላንቴሽን የሽያጭ እቅዱን ሙሉ በሙሉ አሳክቷል፡፡ ከኢትዮ አግሪ ሴፍት በቀር በሁሉም ኩባንያዎች ካለፈው አመት የተሻለ ሽያጭ አላቸው፡፡
በማኑፋክቸሪንግ ክላስተር ከእቅድ አንጻር ከሞሃ እና ማያ ፒፒ በቀር ሁሉም ከፍ ያለ ሽያጭ ነበራቸው። ካለፈው በጀት አመት ጋርም ሲነጻጸር ከማምኮ በቀር ሁሉም ከፍ ያለ አፈጻጸም አሳይተዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት አመት ከሚድሮክ ኮንስትራክሽን እና ሚድሮክ ፋውንዴሽን በቀር ሁሉም ኩባንያዎች ከዕቅድ በላይ አትርፈዋል፡፡ ካባለፈው አመትም የተሻለ አፈጻጸም አሳይተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ 263 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ከዕቅዱ 136 በመቶ እና ካለፈው ዓመት 39.6 በመቶ ብልጫ አለው። 75 በመቶ የሚሆነው የውጭ ምንዛሬ የተገኘው ከማዕድን ዘርፍ ነው።
1.1 ቢሊዮን ብር ለማህበራዊ አገልግሎት ወጪ ተደርጓል። ይህም አራት የዳቦና ዱቄት ፋብሪካዎችን ለማጠናቀቅ፣ ለምግብ ማዕከላት፣ ለኩላሊት እጥበት ማሽን ግዢ እና ለሌሎች ማህበራዊ ግንባታዎች የዋለ ነው።
በቋሚነት፣ በኩንትራት እና በጊዜያዊነት ተቀጥረው ለሚሰሩ ከ79 ሺህ በላይ ለሚሆኑት ሰራተኞቹ ለደሞዝ ብቻ 6.9 ቢሊዮን ብር ወጪ አድርጓል። ” ብለዋል።

