ከፍተኛ የአገር መከላከያ አዛዦች ያላቸውን ግብአቶችና አቅም በመጠቀም አሰብን በማስመለስ በቁጭት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም እንደሚያስከብሩ እየተናገሩ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ የባህር ኃይል በማናቸውም ሰዓት የባህር ስፍራውን ለመያዝ ዝግጁ እንዲሆን ታዘዘ። ጠቅላይ ሚኒስትር የፈረሰውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዳግም ሲገነቡ የባህር ኃይሉም ዳግም እንዲወለድ ሲያደርጉ “ባህር ሳይኖር” በሚል በርካታ “ኢትዮጵያዊያን” ነን የሚሉ ሲተቹ እንደነበር ይታወሳል።
ሰሞኑን ባልተለመደ ሁኔታ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር አዛዦች አሰብ በግፍ የተወሰደ የኢትዮጵያ ንብረት መሆኑን በመጥቀስ አስፈላጊውን ሁሉ ዋጋ በመክፈል እንደሚያስመልሱ መናገራቸውን ተከትሎ ባህር ኃይሉ እንዲዘጋጅ መታዘዙ አነጋጋሪ ሆኗል። “በባዶ ሜዳ የባህር ኃይል” ሲሉ የነበሩ በይፋ አሳባቸውን አልቀየሩም። ይልቁኑም ለሻዕቢያ በመቀገን “ውጊያ ከተነሳ ለኤርትራ አግዙ” ሲሉ ተሰምቷል።
እነዚህን ቡድኖች ” ባንዳና ልክስክስ” በማለት የጠሯቸው የአገር መከላከያ ከፍተና አዛዦች በሙሉ ልብ አሰብን እንደሚያስመልሱ መናገራቸው ከአባይ ግድብ መገደብ ጋር አንድ ላይ ሰፊ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል። አጅንዳውም ህዝባዝዊ ከመሆን አልፎ የመከላከያ አባላት ” ይምንሞትበት ምክኛት አለን። ምክኛቱም ክብራችን ነው” በሚል በግል አሳባቸውን እየሰጡ ነው።
ኢትዮጵያ የባህር በር እንዳታጣ ታሪክ የሰሩ ከፍተኛ የጦር ጀነራሎች፣ ባለከፍተኛ ማዕረግ ወታደሮችና፣ በድፍኑ “የደርግ ወታደር” ተብለው ሜዳ ላይ የተጣሉትን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባለትና ሞትና እንግልት፣ ውርደትና ስቃይ ዳግም ያደሰው ይህ ዜና በስፋት እየተሰራጨ ባለበት በዚህ ወቅት በባህር ኃይል ዋና ማዘዣ ምርቃት ላይ የተሰጠው መመሪያ በጉጉት የሚጠበቅ ሆኗል።
“አሰብ የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ግዛት ነው የኢትዮጵያም ህልውና ነው” በማለት ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ ሰሞኑን መናገራቸው ይታወሳል። ይህንን ሲሉ ያነሱት ዋና ጉዳይ የአሰብ ወደብ የተወሰደው በኢትዮጵያ ጉዳይ የመወሰን መብት ባልነበረው የሽግግር ቡድን አማካይነት መሆኑ በመጥቀስ ነበር።

የመከላከያ የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹ፣ አራት መሰረታዊ የህግ አግባብ በማንሳት ሲናገሩ በዲፕሎማሲው አገባብ ጉዳዩ እንዳለቀ ከፍንጭ በላይ ይፋ አድርገዋል።
ለውዳጆች አሰብ እንዴት እንደተወሰደ፣ ታርካዊ ዳራውን፣ ኢትዮጵያ ከባህሩ ያላትን ርቀትና ዓለም ዓቀፍ ህግ በማጣቀስ አሰብ ወደ ባለቤቶቹ እንደሚመለስ በገሃድ መናገራቸውን ተከትሎ አሰብን በድንግዝግዝ የያዘው ሻዕቢያ በቀጠራቸው “ኢትዮጵያዊያን” አማካይነት የበኩሉን ምላሽ እየሰጠ ነው።
ወታደራዊው ዲፖሎማቱ በርካታ አገራት “በእናንተ ድክመት ነው እስካሁን ያልተመለሰው እንጂ እስካሁን መቆየት ያልነበረበት ነበር ይሉናል”ብለዋል።”በአሁን ወቅት ቀይ ባህር የህልውናችን ጉዳይ ሆኗል። ለህልውናችን ስንልም የትኛውን ዋጋ ከፍለን አሰብን እናስመልሰዋለን” በማለት ለኢትዮጵያ የባህር በር ሲሉ ህይወታቸው ያለፉትን የኢትዮጵያ ውድ ልጆች አጥንትና ደም ከመቃብር የሚጣራ መልዕክት አስተላልፈዋል። ከአባይ ወንዝ መገደብ ደስታና ፈንጠዝያ ጋር ተያይዞ ሕዝብም በድጋፍ ንግግራቸውን በማህበራዊ ሚዲያ እየተከፋፈለውና እያጋራው ይገኛል።
” አሰብ የባህር በራችንን ወደ እናት ሃገሩ ኢትዮጵያ ለመመለስ ለሚሰጠን ግዳጅ ሙሉ በሙሉ ተዘጋጅተናል ።” ሲሉ ሌላኛው ብርጋዴል ጀነራል ቡልቲ ታደሰም በይፋ ከዲፕሎማሲው አግባብ በዘለለ ዝግጁነታቸውን አስታውቀዋል።
ጀነራሉ “አሰብ የባህር በራችንን ለማስመለስ በመቁረጣችን የሚከፋው ካለ ይክፋው፤ ጠላት ያጨበጭብልናል ብለን አይደለም የባህር በር ፋይልን የመዘዝነው፣ የራሳችን የሆነውን የባህር በራችንን የምናስመልሰው ሰላም በማጣታችን ምክንያት ፣ የኢትዮጵያ የመኖር ያለመኖር ህልውናችን ጉዳይ ስለሆነ ነው ፤ ይህንን ጉዳይ ጠላቶቻችን ማስቆም እንደማይችሉ ተገንዝበዋል ” ብለዋል።
“የአሰብ ወደብና ቀይ ባህርን ወደ እናት አገራቸው ኢትዮጵያ ለመመለስ ለሚሰጠን ግዳጅ ሙሉ በሙሉ ተዘጋጅተናል” በማለት የኢትዮጵያን ጉድለት ለመሙላት፣ የኢትዮጵያዊያንን ውርደት ለመካስ አገር መከላከያ ቁርጠኛ መሆኑ ጀነራሉ አመልክተዋል።
“ከ33 ዓመታት በኋላ ዳግም ወደ ሃይልነት ስለተመለሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” በማለት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የደስታ መግለጫ ሲያሰሙ ለኢትዮጵያ የባህር ኃይል መመሪያ አስተላልፈዋል።
ዳግም ወደ ነበረበት ቀይ ባህር እንደሚመለስ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ዋና መስሪያ ቤት ሲመረቅ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ የዋና መስሪያ ቤቱን ቁልፉ ለኢትዮጵያ ባህር ሃይል አዛዥ ሪል አድሚራል ክንዱ ገዙ አስረክበዋል።
“ግዙፍና ውብ የሆነው የባህር ሃይላችን ዋና መስሪያ ቤት መከላከያ ሪፎርሙን በቁርጠኝነት መተግበር የመቻሉንና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም አስጠባቂ ተቋማትን እውን ማድረግ የመቻሉን ብቃት የሚመሰክር ነው” ሲሉም አስታውቀዋል።
“የባህር ሃይል አመራርና አባላት ከ33 አመት በኋላ ቁጭት ሻሪ ሃይል ሆናችሁ በመምጣታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ” ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ “በማንኛውም ጊዜ የባህር ስፍራችሁን ለመያዝ ዝግጁ ሁኑ” የሚል መመሪያ ሰጥተዋል።
ሀገራችን በሴራ ከተገፋችበት ቀይ ባህር መመለስ ስለሚገባት የኢትዮጵያ ባህር ሃይል መስሪያ ቤት በፍጥነት መገንባት እንዳለበት አቅጣጫ የሰጡት ፊልድ ማርሻል መሆናቸውን የጠቆሙት የመከላከያ መሀንዲስ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አብቼ በበኩላቸው “በሁለት ዓመት የተሰጠንን ተልዕኮ በ1 ዓመት ተኩል አጠናቀን ማስረከብ መቻላችን የነበረንን ቁጭት ያሳያል” ሲሉ የአሰብን ጉዳይ በተመሳሳይ ስሜት አሳይተዋል።
የባህር ሃይል ዋና መስሪያ ቤት ውጭ በቢሾፍቱም የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ማሰልጠኛ ማዕከል መመረቁም ይታወሳል። ይህም ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህር ለምታደርገው ግስጋሴ አንዱና ትልቁ የሰው ኃይል ማዘጋጃ ማዕከል ይሆናል።

