ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ምርጫ ቦርድ አውሮፓ ህብረትን ሳይጨመር ከሰባት ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማግኘቱን አስታወቀ። በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሰማሩ ምርጫ አስፈጻሚዎች ” በወቅቱ ክፍያችን አልተፈጸምም ” በሚል ያቀረቡት ቅሬታ ትክክል መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።
ከነዚህ ምርጫ አስፈጻሚዎች መካከል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተሰማሩት ፥ ” የክፍያ መንጠባጠብ አለ ፤ በዚህ ምክንያት ብዙ ዛቻ ፣ ማስፈራርያና ስድብ እየደረሰብን ነው ” ሲሉ ከዚህ ቀደም ቅሬታቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች ገልጸው ነበር። ይህንኑ አስመልክቶ ምርጫ ቦርድ በትናንትናው ዕለት ምላሽ ሰጥቷል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሮ ሜላትወርቅ ሀይሉ፣ ” እስካሁን ድረስ ተንጠባጥቦ የቀሩ ያልተከፈሉ አሉ። ለአብዛኛው ክፍያ ተከናውኗል ” ብለዋል። ምክንያቱንም ሲያስረዱ ውሉ አንድ አስፈጻሚ የምርጫ አስፈጻሚ ሆኖ፣ ስልጠና ወስዶ፣ ሥራ ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ በተጠናቀቀ በ15 ቀን ውስጥ ቦርዱ መክፈል እንዳለበት ይደነግጋል።
ውሉ በሚያዘው መሰረት ክፍያ ለመፈጸም የምንጠቀመው የባንክ አካውንቱ ከቦርዱ ውል የገባው አስፈጻሚ አካል ወይም ግለሰብ አካውንት ቁጥር ቢሆንም ተከፋዮቹ የእናት፣ የአባት..አካውንት ሰለሚልኩ የአሰራር ችግር መፈጠሩን አመልክተዋል። “ውሉ የሌላ፣ አካውንቱ የሌላ ነው። ስለዚህ ለሌላ ሰው ብር መስጠት አንችልም” በማለት አሰራሩ ላይ የተፈጠረውን ችግር አስረድተዋል። በዚህ ምክንያት ክፍያ የተያዘባቸው አሉ።
“የባንክ አካውንት ብቻ ሳይሆን ስልክ ቁጥርም እየተሳሰረ ነው። የሚሰጡን ስልክ ቁጥሮች በውሉ ላይ የሚሞሉትና ከባንክ ጋር የሚተሳሰሩት የተለያዩ ናቸው። ይህንን የማጥራት ሥራ መስራት አለብን።” ሜላት ወርቅ አሰራሩን ያወሳሰበውን ጉዳይ አመልክተዋል።
“በሶማሌ ክልል ደግሞ አካውንት የሌላቸው አሉ። በአፋርም የተወሰኑ አሉ። ስለዚህ ይህንን አጥርተን እጅ በእጅ የሚከፍሉ ሠራተኞች በሶማሌ ክልል ልከን በካሽ እጅ በእጅ እየከፈልን ነው ” በማለት ቦርዱ የሚችለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል፣ “ቦርዱ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ምን ያክል የገንዘብ ድጋፍ አገኘ ? ምን ስራ ላይ አዋለው ?” ተብለው የተጠየቁት ወ/ሮ ሜላትወርቅ፣ በተመድ ስር ካሉ ከስፔይን፣ አየርላንድ፣ ኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ እንግሊዝ፣ ጃፓን ወደ 7 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አግኝተናል ” ብለዋል። በአውሮፓ ህብረት በኩል ጨምሮ ሌሎች የሰጧቸው የድጋፍ መጠን የሚታወቀው ምርጫውን ሲጠናቀቅ መሆኑን አስረድተዋል።



