የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንና ኦቪድ ግሩኘ የፒያሳ መልሶ ማልማት አካል የሆኑ ዘመናዊ የንግድ ሞሎችንና የመኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል እና የኦቪድ ግሩኘ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ ተፈራርመዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱ የፒያሳ መልሶ ማልማት አካል በሆነው 9 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ አራት ግዙፍ የንግድ ሞሎችንና የመኖሪያ ቤት ግንባታን ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ በማጠናቀቅ ለማስረከብ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
ስምምነቱ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የንግድ ሱቆችን፣ ሞልና መዝቦልድ ሞል እንዲሁም የጣይቱ የመኖሪያ አፓርትመንት በአልሙኒየም ወርክሾፕ ቴክኖሎጂ ሰርቶ በተያዘው የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ መሆኑ ተጠቅሷል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል፥ ኦቪድ ኩባንያ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በሥራ ላይ እያዋለ የሚገኝ ተቋም በመሆኑ ስምምነቱን ታሪካዊ ያደርገዋል ብለዋል።
ስምምነቱም የመንግሥትና የግል አጋርነት ትብብርን በማሳደግ አዲስ የሥራ ባህል እንዲፈጠር የሚያደርግ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል።
ኦቪድ በሦስት ወራት ውስጥ እጅ አጠር ለሆኑ ዜጎች ቤትን ገንብቶ በማስረከብ፤ ከተሰራ ለውጥና ስኬት ማምጣት እንደሚቻል ያስመሰከረ ኩባንያ መሆኑን ተናግረዋል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በፒያሳ መልሶ ልማት የሚያስገነባቸውን የንግድ ሞልና መኖሪያ ቤቶችም በፍጥነትና በጥራት አጠናቆ እንደሚያስረክብ እምነታቸው መሆኑን ገልፀዋል።
የኦቪድ ግሩኘ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ፤ ኩባንያቸው ፕሮጀክቶቹን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አጠናቆ ለማስረከብ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በቀጣይም የኦቪድ ኩባንያ ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር ያለውን ትብብር በማጠናከር በግንባታው ዘርፍ የበኩሉን ገንቢ ሚና እንደሚወጣ ገልፀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
press.et


