ቪኦኢ ዜና – 8.3 ትሪሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅስ ግዙፍ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ገበያ በርዎ ላይ ቢመጣ ምን ያደርጋሉ? የብሪክስ አባል የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ይህንን ታላቅ የኢኮኖሚ ማዕበል በብቃት ለመቀበል የሚያስችላትን ስትራቴጂካዊ መሠረት ባለፉት ስምንት ዓመታት በተጨባጭ ጥላለች።
ፊውቸር ማርኬት ኢንሳይትስ (FMI) ይፋ ያደረገው አዲስ ጥናት እንደሚያመለክተው፣ በሀገር ውስጥ ጉዞ መነቃቃት፣ በዲጂታል መድረኮች መስፋፋት እና በቅርስ ቱሪዝም ሳቢያ የብሪክስ ሀገራት የቱሪዝም ኢኮኖሚ በአውሮፓውያኑ 2036 ወደ 8.3 ትሪሊዮን ዶላር ግዙፍ የገበያ ዋጋ ያድጋል።
የዚህ ታላቅ ጥምረት አባል የሆነችው ኢትዮጵያም፣ በመደመር እሳቤ ባለፉት ስምንት ዓመታት የወሰደቻቸው የፖሊሲ ሪፎርሞችና ያስመዘገበቻቸው አስደማሚ ስኬቶች፣ ከዚህ ዓለም አቀፍ ሀብት ቀጥተኛ ተጠቃሚ የምትሆንበትን አዲስ የኢኮኖሚ ምዕራፍ ከፍተውላታል።
ቱሪዝምን ከተራ ተቀጥላ ዘርፍነት አውጥቶ ከአምስቱ አሀገራዊ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ ማድረጉ ደግሞ ዛሬ ላይ ለተመዘገቡት ተጨባጭ ድሎች ዋነኛ መሠረት ሆኗል።
በእነዚህ የለውጥ ዓመታት ውስጥ የቱሪስት ፍሰት እና የታሪካዊ ገቢ እምርታው አስገራሚ ስኬት አስመዝግቧል። የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር ታሪካዊ ጣሪያውን ሰብሮ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ይህ አሃዝ ከማይስ (MICE – የስብሰባ፣ ማበረታቻ፣ ኮንፈረንስ እና ኤግዚቢሽን) ቱሪዝም ጋር ተዳምሮ ከ5.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማስገኘት ችሏል።
በሌላ በኩል 60 በመቶ የሚሆነውን የብሪክስ የሀገር ውስጥ ጉዞ አዝማሚያ የተከተለችው ሀገራችን፣ በሀገር ውስጥ 50.16 ሚሊዮን ዜጎችን በማንቀሳቀስ 79 ቢሊዮን ብር የሚገመት እጅግ ግዙፍ የውስጥ የገንዘብ ዝውውር መፍጠር መቻሏ የዘርፉን አቅም በግልጽ ያሳያል።
ይህ ታላቅ ስኬት በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን፣ ትኩረት በተሰጣቸው ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የተገነባ ነው።
የአንድነት፣ የእንጦጦ፣ የወንጪ፣ የጎርጎራ እና የኮይሻ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም የመዲናዋን እና የበርካታ ከተሞችን ገጽታ ሙሉ በሙሉ የለወጠው የኮሪደር ልማት ለዚህ ስኬት የጀርባ አጥንት ናቸው።
በተጨማሪም የዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ የታሪካዊ ቤተመንግሥታት ታድሰው ለሕዝብ ክፍት መሆን፣ እና 7 አዳዲስ ዘመናዊ የክልል ኤርፖርቶች መገንባታቸው የመዳረሻዎችን አድማስ አስፍተዋል።
ከዚህም ባለፈ የፀሐይ አውሮፕላንን ጨምሮ ከ35 በላይ የተዘረፉ ቅርሶችን ወደ ሀገር ቤት ማስመለስ መቻሉ፣ እንዲሁም የላሊበላ፣ የጀጎልና የፋሲል ግንብ ጥገናዎች የባህል ዲፕሎማሲውን ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረውታል።
ወደፊት ከብሪክስ ሀገራት የቱሪዝም ዕድገት (በተለይ ከደቡብ አፍሪካ 6.2 በመቶ እና ከሕንድ 5.8 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት) ጋር ይበልጥ ተዋሕደን ድርሻችንን ለማሳደግ የዲጂታል አካሄድ የግድ ይለናል።
ከ55 ሚሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉትን የቴሌብር ሥነ-ምህዳር ወደ ስማርት የቱሪዝም መተግበሪያዎች በማሳደግ የዲጂታል ክፍያ ትስስርን ማጠናከር ቀዳሚው ተግባር ሊሆን ይገባል።
በተጠናቀቀው ዓመት ከተስተናገዱት 204 ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በመነሳት የማይስ (MICE) ቱሪዝምን በክልሎች ማስፋፋት፣ እንዲሁም የ”5 ሚሊዮን ኮደርስ” ንቅናቄን ለዲጂታል ቱሪዝም ማዋል ሀገራችን ከብሪክስ የቱሪዝም ማዕበል የብሔራዊ ክብር ከፍታዋን እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን በተጨባጭ እንድታረጋግጥ ያደርጋታል።
በሰለሞን ገዳ

