ትራምፕ ማሸነፍ በተለይ ከክሪፕቶከረንሲ ጋር ግንኙነት ያላቸው ባለጠጎች ሀብት እንዲመነደግ አድርጓል። ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት መሆናቸው መነገሩን ተከትሎ የአለማችን ቢሊየነሮች ሀብት ተመንድጓል።
ፎርብስ ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ትራምፕን የደገፈው ኤለን መስክ በአንድ ቀን ብቻ 21 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ሀብት ማግኘቱን አመላክቷል።
ሽንጡን ገትሮ የተከራከለትና በየመድረኩ የተናገረለት ትራምፕ ማሸነፍ የቢሊየነሩን አጠቃላይ ሀብት 285.6 ቢሊየን ዶላር አድርሶት የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር እንዲሆን አድርጎታል።
ለዚህም የቴስላ የአክሲዮን ዋጋ በ15 በመቶ መጨመር ዋነኛው ምክንያት ነው ብሏል ፎርብስ በዘገባው። ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን 120 ሚሊየን ዶላር መለገሱ የሚነገርለት ኤለን መስክ፥ ጥቂት ሰጥቶ ብዙ በብዙው ማትረፍ ችሏል።
ትራምፕ ዳግም ወደ ዋይትሃውስ ከገቡ ለመስክ የመንግስት ስልጣን እንደሚሰጡ መናገራቸው የሚታወስ ነው። በሪፐብሊካኑ እጩ ማሸነፍ ኤለን መስክ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአለማችን ቀዳሚ ባለጠጎችም በአንድ ቀን ሀብታቸው በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
በተለይ ከክሪፕቶከርንሲ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቢሊየነሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጸው ፎርብስ፥ ትራምፕ በቅስቀሳቸው የክሪፕቶከረንሲ ታክስ እቀንሳለሁ ማለታቸውን አስታውሷል።
ጄፍ ቤዞስ – ቤዞስ የትራምፕ ድል 7 ቢሊየን ዶላር አስገኝቶለታል። የአማዞን አክሲዮኖች ሽያጭ በ3.8 በመቶ ማደጉም የቤዞስን ሀብት 223.5 ቢሊየን ዶላር አድርሶት ከመስክ በመቀጠል የአለማችን ሁለተኛው ቢሊየነር ሆኗል።
Bruk

