የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ስጋትን እና ሌሎች አዋኪ ድርጊቶችን በጥናት በመለየት የህብረተሰቡን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ ተከታታይ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ይህንኑ እርምጃ የመውሰድ ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል በተለያዩ ጊዜያት በህጋዊ ንግድ ሽፋን ጫት የማስቃምና ሺሻ የማስጨስ ህገ ወጥ ተግባር ከሚፈፀምባቸው ንግድ ቤቶችና መኖሪያ ቤቶች የተሰበሰቡ 7ሺህ 223 የሺሻ ማጨሻ እቃዎች፣ ከ4 ኪሎ ግራም በላይ አደንዛዥ ዕፅ እና የተበላሸ ቅቤ ተወግዷል፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ደመና ተስፋዬ እንደገለጹት የሺሻ ዕቃዎቹ የተሰበሰቡት ለተከታታይ 4 ወራት በመኖሪያ ቤቶች፣ በንግድ ቤቶች፣ በጭፈራ ቤቶች እና በፔንሲዮኖች በአጠቃላይ በ210 ቤቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተሰራ የኦፕሬሽን ስራ ነው።
ወንጀል ፈፃሚዎች ወንጀል ለመፈጸም የሚዘጋጁበትም ሆነ ወንጀል ከፈጸሙ በኋላ የሚደበቁበት አንዱ ሺሻ ቤት በመሆኑ እንዲህ ዓይነት የወንጀል መንስኤዎችን እየተከታተሉ እርምጃ የመውሰዱ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ረዳት ኮሚሽነር ደመና ገልጸዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ታዬ ሽፈራው በበኩላቸው የከተማችንን ሠላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ የሚከናወነውን ተግባር በመደገፍ በኩል የህብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ለወንጀል መፈጸም መንስኤ የሚሆኑ ድርጊቶችን ሲመለከት መረጃና ጥቆማ የመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ደንብ ማስከበር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳኜ ሂርጴሳ ለአዲስ ፖሊስ እንደገለፁት የህብረተሰቡን ጥቆማ መነሻ በማድረግና በጥናት በመለየት አዋኪ ድርጊቶችን ለመከላከል ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ስራዎች እየተሰሩ ነውም ብለዋል።
ዘገባ፡- ረዳት ሳጅን አለም ልጅአለም via Addis Abeba police


