ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ዘርፈ ብዙ ችግሮች አሉባቸው ተብለው ከሚጠቀሱት ተቋማት መካከል የጤና ተቋማት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተለይ የግል የሕክምና ተቋማት ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በርከት ያሉ ናቸው። እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የግል ጤና ተቋማት ለሚሰጡት አገልግሎት እየጠየቁ የሚገኙት ዋጋ አይቀመስም።
በተለይ በሆስፒታል ደረጃ አገልግሎት የሚሰጡ የግል ተቋማት አልጋ ይዞ ለመታከምም ሆነ ለሌሎች የሕክምና አገልግሎቶቻቸው ከካርድ ጀምሮ የሚጠይቁት ዋጋ በምን ዓይነት ስሌት ተሰልቶ የሚጠየቅ እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
ይህ በተደጋጋሚ የሚስተዋል ከመሆኑም በላይ ለተመሳሳይ አገልግሎቶች በተለያዩ ሆስፒታሎች የሚጠየቁ ገንዘቦች ወጥነት አይታይበትም። እና ህክምና ንግድ ወይስ አገልግሎት ነው ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች ጠይቀናል።
የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስቱ ዶክተር መኮንን ነጋሽ እንደሚሉት ህክምና ከንግድ በላይ ሰዋዊነትን ትኩረቱ ያደረገ ዘርፍ ነው ።
በጤና ተቋማት አስተዳደር ላይ የረጅም ጊዜ ልምዳ ያላቸው ዶክተር ግርማ አባቢ በበኩላቸው የህክምናው ዘርፍ ከንግድ ይልቅ ለህብረተሰብና ለአካባቢ ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጥ ስራ ነው።
ይህም ማለት ተቋማቱ ደንበኞቻቸው ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩት የሚሰጡትን የጤና አገልግሎት አሰጣጥና ጥራት የተገልጋዮች እርካታን በማሳደግ እንደሆነ ነው ዶክተር ግርማ የገለጹት።
ዶክተር አታክልቲ ጸጋይ በበኩላቸው፣ በህክምና ቁሳቁስና ግብዓት ላይ የሚታየው የዋጋ አለመረጋጋት፣ የውጭ ምንዛሪ ጉዳይ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች የዘርፉ ፈተናዎች ናቸው። እነዚህን ጉዳዮች ታሳቢ በማድረግ የህክምና ዋጋ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ይገባል። እዚህ ላይ ህብረተሰቡን ታሳቢ ያደረገ መሆንም አለበት።
ይህ የማይደረግ ከሆነ የህክምና ተቋማቱ ቀጣይነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይወድቃል። ከዚህ መርህ ውጪ የሚሰሩ የህክምና ተቋማት አይጠፉም። ስለዚህ የህክምና ወጪዎችን ተመጣጣኝ በማድረግ አገልግሎቱን ማስቀደምና ሰዋዊነትን ትኩረት ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።
እንደ ዶክተር አታክልቲ ገለፃ፤ በህክምና ሥነ ምግባር በታካሚዎች ዘንድ እምነትን መፍጠር የመጀመሪያው ሥራ ነው። “መታመን ለራስ፤ መታመን ለታካሚ” ነው። ህክምና የራሱ የሆነ የሙያ ሥነ ምግባር አለው። በኢትዮጵያ የግል ህክምና ተቋማት ውስጥ በዋጋ ዙሪያ የሚታየው ክፍተት ከሌሎች ሀገራት አንፃር ሲታይ የተሻለ ነው። ለዚህም ምክንያቱ የማህበረሰቡ ባህል፣ አመለካከትና እምነት ነው።
በሳሙኤል ወንደሰን
Via gazetteplus

