ብሔራዊ ባንክ በሕጋዊና ትይዩ ገበያው መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሬ ልዩነት በመሰረታዊነት የማጥበብ እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ። የብሄራዊ ባንክ ገዢ መንግስት የጀመረውን ጥብቅ የፋይናንስ ሰርዓት ጠብቆ ልዩነቱን ለማጥበብ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የባንኩ የሪፎርም አንደኛው ዓላማ በሕጋዊና በትይዩ ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብና የጥቁር ገበያውን እንቅስቃሴ ማዳከም መሆኑን በማውሳት፥ አሁንም ልዩነት በመኖሩ ባንኩ ይህን ለመፍታት እየወሰደ ስላለው እርምጃ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በሰጡት ምላሽ፥ በሕጋዊና በትይዩ ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት በመሰረታዊነት ለመፍታት ጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ እየወሰደ ስለመሆኑ አብራርተዋል።
በትይዩ ገበያው ላይ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት እንዲጨምር አድርጎት የቆየው፥ አስመጪዎች የቅድመ ክፍያ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ለሚያቀርቡት ጥያቄ የሚፈቅድ የባንክ አሰራር ስላልነበር ነው ብለዋል።
ብሔራዊ ባንክ በአሁኑ ወቅት አስመጪዎች የቅድመ ክፍያ የውጭ ምንዛሬ ጥያቄ በሚያቀርቡበት ጊዜ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የባንክ አሰራር መመሪያ በማውጣት እየተገበረና ውጤት እያመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ባንኮች ለውጭ ምንዛሬ ጥያቄ የሚሰጡት የዘገየ ምላሽና ለውጭ ምንዛሬ የሚያስከፍሉት ተጨማሪ ክፍያ ዜጎች ወደ ትይዩ ገበያው እንዲሄዱ ሲያስገድዳቸው መቆየቱን ነው የገለጹት።
ይሁንና ብሔራዊ ባንክ ለዚህም መፍትሄ ማስቀመጡን በመጥቀስ፥ ባንኮች ለውጭ ምንዛሬ አቅርቦት የሚያስከፍሉት ክፍያ ከአራት በመቶ እንዳይበልጥ መደረጉን አንስተዋል።
የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግና አጠቃቀም ላይ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ ስራዎች ቢከናወኑም አሁንም የውጭ ምንዛሬ በቀላሉ ማግኘት አዳጋች መሆኑንም ነው ቋሚ ኮሚቴው ያነሳው።
ይህ ደግሞ በህገወጥና ብልሹ አሰራር ምክንያት እየተፈጠረ ያለ ችግር መሆኑን በማንሳት፥ ብሔራዊ ባንክ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምን እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ጥያቄ ቀርቧል።
የባንኩ ገዥ ማሞ ምህረቱ የውጭ ምንዛሬ ችግር እንዳለ በማስመሰል ህገወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አንዳንድ የባንክ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ላይ ባንኮች የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ ክትትል እያደረገ ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ ለችግሩ ዘላቂና አፋጣኝ ስርዓት መዘርጋቱን ጠቅሰው፥ ብሔራዊ ባንክ ባንኮች ግልጽ የውጭ ምንዛሬ አመዳደብና የስጋት አስተዳደር መመሪያ አውጥተው እንዲተገብሩ መመሪያ መስጠቱን ገልጸዋል።
በምክር ቤቱ የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሳለኝ ወዳጆ በሪፎርሙ የውጭ ምንዛሬ ልዩነቱን ለመቆጣጠር እስካሁን የተወሰዱ እርምጃዎች በጥንካሬ የሚወሰዱ ናቸው ብለዋል።
አሁንም ቢሆን በህጋዊ እና በትይዩ ገበያው መካከል ያለውን የምንዛሬ ልዩነት በመሰረታዊነት ለማጥበብ እርምጃዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።

