ኢራን ለእስራኤል የስለላ ድርጅት ሞሳድ ሲሰልል ነበር በማለት በቁጥጥር ስር አውላው የነበረውን ዜጋዋን ዛሬ በሞት መቅጣቷን የኢራን መንግሥት የዜና አውታር ኢርና ዘግቧል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትራምፕ የአያቶላህ አሊ ኻሚኒ ነፍስ መታደጋቸውን ይናገራሉ።
ለሞሳድ ሲሰልል ተገኘ የተባለው ኢስማኢል ፌክሪ አሚር ነው። ኢስማኢል የሞሳድ ወኪልና ከሌላ የእስራኤል ሰላይ ጋር በመገናኘት ምስጢራዊ የሆኑ የኢራን ቦታዎችን የሚመለከትና ሌሎች ቁልፍ መረጃዎችን ለእስራኤሉ የስለላ ድርጅት በማቀበል ተጠርጥሮ በዲሴምበር 2023 በቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበር ነው ዜናው ያመለከተው።
እንደ ኢርና ዘገባ፥ ተጠርጣሪው በኢራን መንግሥት የቀረበበትን ክስ ከማመኑም በተጨማሪ ለዚሁ ሥራው በክሪፕቶከረንሲ ክፍያ መቀበሉ በማስረጃ ተረጋግጧል።
ተጠርጣሪው በጠላትነት የተፈረጀች ሀገርን በመርዳትና የኢራንን ብሔራዊ ደህንነት አደጋ ላይ በመጣል ተከሶ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ በዛሬው ዕለት በስቅላት መቀጣቱን ዘገባው ጠቅሷል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ “ባይቃወሙ ኖሮ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ በእስራኤል ሊገደሉ ነበር” ተባለ።
እስራኤል በዕቅዷ መሰረት የኢራኑን ሁለንተናዊ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒን የመግደል አጋጣሚውን አግኝታ እንደነበር እየተነገረ ነው። ነገር ግን ዶናልድ ትራምፕ “አግባብ የሌለው ውሳኔ ነው ሲሉ በመቃወማቸው ሁሉም ነገር ሰላም ሆኗል” ተብሏል።
ሶስት የአሜሪካ ባለስልጣናትን ዋቢ ያደረገው ሮይተርስ የዜና ወኪል ሪፐብሊካኑ ትራምፕ ኻሚኒን መግደል ጥሩ ሀሳብ አይደለም በሚል መቃወማቸውን አስነብቧል።
ትራምፕ እንዲህ ዓይነቱን ሀሳብ ውድቅ ማድረጋቸው በተገለጸበት አጋጣሚ ኔታንያሁ እና ሪፐብሊካኑ ባለፈው ሳምንት ሰኞ፣ ሐሙስ እና ቅዳሜ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለሶስት ጊዜ ያህል መነጋገራቸውም ተሰምቷል። በአሜሪካ እና ኢራን መካከል ግን ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ንግግር ባለፈው ሳምንት እንዳልነበር ተወስቷል።
ዶናልድ ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ሚዲያቸው ላይ “እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ስትሰነዘር ዕውቅናው አልነበረንም’’ ቢሉም ኔታንያሁ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ከአሜሪካ ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል። ትራምፕም ቢሆኑ የሚሰጧቸው አስተያየቶች በጉዳዩ ላይ እንዳሉበት አሳብቆባቸዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን እና እስራኤል ጦርነቱን ማቆም አለባቸው ፥ይህንም በአፋጣኝ ያደርጋሉ የሚል ሀሳብም ሰተዋል። ዘገባው የሲ ኤን ኤን እና ሲ ቢ ኤስ ኒውስ ነው።

