ሃዲስ ዓለማየሁ ተነሱ። “ሃዲስ ዓለማየሁ አክቲቪስት ሰበር ዜና ብቻ ቢጽፉስ?” ጥያቄ ሆኑ። በበዙ ድካም፣ ራሳቸው ቀልጠው፣ ጧፍ ኩራዝ አቃጥለው፣ ታይፕ ቀጥቅጠው ያስቅመጡት ቅርስ ዛሬ ድረስ መማሪያ መሆኑ ተወሳ። ዛሬ ያሉ ሙያተኞችም ይህን ተከትለው ለመጪው ትውልድ ዳራቸውን እንዲያኖሩ አሳብ ተሰጠ። ” ሰበር እፍ እፍ ነው” ተባለና አቅም ያላቸው አርቲስቶች “እፍታ” ውስጥ ገብተው ቀርተዋል። በሚል ምሳሌ ተጠቅሶ ተነገረ፤ ይህ የተሰማው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከአርቲስቶች ጋር ሲወያዩ ነበር።
ይህ በተሰማ ማግስት ነው በርካታ “ሰበር” ዜናዎች የተሰሙት። ጃዋርና ኤሊያስ መሰረት ሲቀሩ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ማህበራዊ ሚዲያውንና ዩቲዩቡን ያጨናነቀው የሰበር ዜና፣ በስፋት ካቀረቡትና ካጋሩት መካከል አክቲቪዚም ላይ የተሰማሩ “ባለሙያዎችም” ይገኙበታል።
“ውጥረቱ ጨምሯል” ይላል አንዱ የሰበር ዜና አጋሪ ስንታየሁ ቸኮል። “ውጥረቱ ጨምሯል ከፍተኛ መረበሽ ይታያል።የአገዛዙ ልሳኖች ትንፋሻቸው እየተቆራረጠ ትላንት አመሻሽ አስራ ዘጠኝ ሰዎችን የጫነች ወታደራዊ ሂሊኮፕተር ጎርጎራ ላይ ልታርፍ እየተጠጋች ሳለ ተመታ መዉደቋን ተናግረዋል። ” ይላል። አክሎም “በውስጧ የነበሩት እነማን ናቸው? በምን ተመታች ? የጉዳቱ መጠን ምንድነው? ለማደባበስ ሩጫው ጦፏል” ሲል ሄሊኮፕተሯ በፋኖ ኃይሎች ተመታ እንደወደቀች ያትታል። ስንታየሁ በህይወት የመትረፍ እድል እንደሌለም አስታውቋል።
ካስመረቃቸው ውድና አስፈላጊ የህክምና ተቋማት አንጻር ዜና መሆን የነበረበትን የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ዘንግተው የሄሊኮተር አደጋ የመርዶ ዜና የበለጠባቸው አየሩን ያጨናነቁት ዜና፣ ዩኒቨርስቲው ሰባኛ ዓመት እና የአጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉን 100ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ምክንያት በማድረግ በአራት ቢሊዮን ብር ወጪ ያስገነባቸውን ፕሮጀክቶች አጠናቆ ማስመረቁን ተከትሎ በተሰማ ወሬ ነው። ወሬው የ”ፋኖ ድል” ተብሎ በሰበር ዜና ማህበራዊ ሚዲያዎች የተበተነው የሄሊኮፕተር አደጋ ሲሆን፣ እንደ ሰበር ዜና አቅራቢዎቹ ሄሊኮፕተሯ የተመታችው በፋኖ ታጣቂዎች ነው።
የተመረቁት 22 ፕሮጀክቶች መካከል በክልሉ ብቸኛ የሆነው የካንሰር ጨረር ህክምና ማዕከል፣ የኦክስጅን ማምረቻ፣ የካላዛር ቤተ-ሙከራ፣ ሰው ሰራሽ እጅና እግር ማምረቻ፣ ፣ የህጻናትና የአዋቂዎች ህክምና ማዕከል፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ ማጎልበት፣ አዲሱ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ህንጻ፣ የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ሬዲዮ ስትዲዮ ፣ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ቁጥር 2 የማህበረሰብ የቅድመ-መደበኛና የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት፣ የአፄ ፋሲል የህዝብ ት/ቤት (G+2)ባለ 12 መማሪያ ክፍል እና (G+1) ቤተ-መፃህፍት ፣ ኮምምፒዩተር ቤተ-ሙከራ ፣ የምድረ-ግቢ ውበት እና የግብርና መካናዜሽን ለአብነት ይገኙበታል።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ታየ አፅቀስላሴ፣ የኢፌድሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክቡር አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል ፕሬዝዳንት የተከበሩ አቶ አረጋ ከበደ፣ ሌሎች የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራን፣ ሰራተኞች፣ ተማሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ዩኒቨርስቲው አስታውቆ ነበር።

ስንታየሁ ስም ሳይዘረዝር ባለስልጣናት ማለቃቸውን ቢገልጽም፣ ዜናውን በቅብብሎሽ ሲያሰራጩ የነበሩ ሟቾችን ስም ጠቅሰው ዜናውን “ሰበር” በማለት ተቀባብለውታል።
ፕሬዚዳንት ታዬ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ዲያቆን ዳንኤል ክበረት፣ አቶ አገኘሁ፣ አቶ አረጋ፣ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት መሞታቸውን ያዘገቡ “ድል ለፋኖ” በሚል ነበር ዜናቸውን የዘገቡት።
“አርበኛ በሉኝ” ያለው መሳይ መኮንን በአንከር ሚዲያ፣ አቶ ነዓምን ዘለቀ በኤክስ ገጻቸው፣ እንዲሁም በርካቶች መንግስትን የሚቃወሙ በስም የሚታወቁና በድብቅ ስም የሚጠቀሙ በቅብብሎሽ፣ መረጃ ፎረም በበርካ ሰበር ዜናዎችን በመጋራት ዜናውን በስፋት ካሰራጩት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። ይህ ከሆነ በሁዋላ ነበር የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አጭር መረጃ የሰጠው።

በለስልጣናቱ ጎንደር የተመረቀ ፕሮጀክት መርቀው፣ ወደ ጎርጎራ ሲያመሩ በሁለተኛው ምድብ የሄሊኮፕተር ጉዞ ላይ የነበሩት ለማረፍ በተቃረቡበት ወቅት በፋኖ ኃይሎች ተመታ ስትከሰከስ ያየ “ፋሲል ሄሊኮፕተሯ ስትወድቅ እንዳትወጡ ተብለን ተከለከልን…” በሚል ለፋሲል የኔ ዓለም ምስክረነቱን እንደሰጠ ተደርጎ ዜናው ቀርቦም ነበር።
“በትናንትናው እለት ሰኔ 08/2017 ዓ.ም በጎርጎራ ሪዞርት በማረፍ ላይ የነበረ ሄሊኮፕተር የቴክኒክ ችግር አጋጥሞት ነበር። በችግሩ ምክንያትም በሰው ላይ ያጋጠመ አደጋ አለመኖሩን የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ። ይህንኑ ተከትሎ ባለስልጣናቱ ከጎርጎራ ወደ ባህር ዳር አምርተው የተለያዩ መሰረተ ልማቶችንና አገልግሎቶችን ሲጎበኙ ታዩ። ይህ እስከሚሆን ድረስ ፋኖ እንደመታት የተነገረላት ሄሊኮፕተር ጉዳይ ከፍተኛ የድል ዜና ሆኖ ነበር።
ይህን መግለጫ ተከትሎ ዜናውን በስህተትም ይሁን ሆን ብለው ያሰራጩ ማስተካከያ፣ ይቅርታ ወይም ማሻሻያ ወይም ማመጣጠኛ አላደረጉም። በዜናው ከባለስልጣንቱ ስራና ኃላፊነት ጋር ግንኙነት የሌላቸው ቤተሰቦች፣ ወዳጆች እንዲሁም ዜጎች ተረብሸው እንደነበር የጠቀሱ በኢትዮጵያ ሚዲያዎችና ማህበራዊ አውዶች እየተለመደ የመጣው ባህል አሳሳቢ መሆኑን ያመለክታሉ።
እነዚሁ ወገኖች አደጋው ተከስቶ ቢሆን እንኳ በዚህ ደረጃ ሰርግና ምላሽ ማድረጋቸው የቀደመ ሞራልና ኢትዮጵያዊ ባህላችንን አደጋ ላይ እንደሆነ የሚያሳይ እንደሆነ አመልክተዋል።
ከምንም በላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽንን የሚወቅሱ በርካታ ናቸው። ችግሩ ወይም አደጋው እንደተፈጠረ ሳይደበቅ በአጭሩ ይፋ ቢያደርጉት የሰበር ዜና ጋጋታም ሆነ እሱን ተከትሎ የሚነሳ መረባበሽ አይኖርም። ከዚህም በላይ መደበቅ የማይቻል ጉዳይ እያፈኑ ትርምስ እንዲፈጠር መፍቀድ ዓላማውም ገልጽ እንዳልሆነ እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ።
“በሁለት መስመር የሆነውን መግለጽ ምን አስቸግሮ ነው አገር የሚናጠው?” የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ እንዲህ ያለው ዳተኝነት አሰራር ከሆነም መንግስት ይፋ ሊያደርግ ይገባል። አለበለዚያ ደግሞ አሰራሩን ዛሬ ነገ ሳይል ሊመረመር ይገባል። ተደጋገመ” በማለት አስተያየት የሰጡ፣ ሚዲያዎችም ቢያንስ ቢያንስ ለማጣራት ጊዜ ቢወስዱ፣ ከተሳሳቱም ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል ሲሉ ቅሬታና የችግሩን መደጋገም አመልክተዋል። አድማኞችም ተመልካቾችም በተደጋጋሚ ስህተት፣ አይን ያወጣ ውሸት ሲቀርብላቸው “ለምን ትዋሻላሽሁ” የሚል ጥያቄ አለማቅረባቸው ለአጥፊዎቹ የልብ ልብ እንደሰጠ እነዚሁ ወገኖች አስታውቀዋል።
ሄሊክፕተርም ሆነ አውሮፕላን አደጋ ሲያጋጥም ኢትዮጵያ የመጀመሪያ አገር እንዳልሆነች የሚገልጹት ደግሞ፣ ሆኖ ከሆነ ከማድበስበስ በይፋ የሆነውን ማስታወቅ ለምን ነውር እንደሆነ በመጠየቅ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ መከተልና፣ ዘመኑ የመረጃ መሆኑን በመገንዘብ አሰራርን ማስተካከል እንደሚገባ ይገልጻሉ።
ከዚህ አደጋ ጋር የተያያዘ ይሁን በሌላ ሳይብራራ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከፍተኛ የካሜራ ባለሙያ የሆነው አቶ ብዙአየሁ ብርሀኑ መኮንን በሥራ ላይ እያለ ባጋጠመው ድንገተኛ አደጋ ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በዛሬው እለት ህይወቱ ማለፉን አመልክቷል።
በሰበር ታጅቦ የቀረበውን “ባለስልጣኖች አለቁ” ዜና ባሰራጩት ክፍሎች ልጥፍ ግርጌ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ያቀረቡት ሽሙጥና የሚያስፈግግ ሲሆን፣ አጥበቀው የተቆጡና የተቹም ታይተዋል። የአስተያየት መስጫ ሳጥናቸውን ቆልፈው ቅስቀሳና መረጃቸውን የሚያሰራጩ እንዳሉ የሚታወቅ ነው።

ባለስልጣናቱ “አለቁ” ከተባለ ብሁዋላ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀሥላሴ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ ሚኒስትሮች እና ሌሎችም መሪዎች በባሕር ዳር ከተማን ሲጎበኙ ታይተዋል።
አሚኮ እንዳለው የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ መሪዎች ባሕር ዳር ከተማ ሲደርሱ የክልሉ ከፍተኛ መሪዎች እና የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የሥራ ኀላፊዎች፣ የከተማዋ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሌሎችም ነዋሪዎች ተቀብለዋቸዋል። ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አንጋፋው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያስገነባቸውን ፕሮጀክቶች ማስመረቃቸውን ለባህር ዳር ነዋሪዎች ነግረዋቸዋል።
“በባሕር ዳር ከተማ ውስጥ በጎርጎራ አምሳል የሚገነባው ጣና ማሪናም ከጎርጎራ ጋር ተደማምሮ ጣና ሐይቅን “የምድር ገነት” የሚያሰኝ ድንቅ ሥራ ነው” ሲሉ አወድሰዋል።
“ጎርጎራ ኢትዮጽያውያን ከፍ ያለ ነገር የምንወድ እና መሥራት የምንችልም እንደኾንን የሚያመላክት ነው” ሲሉም ገልጸዋል። ጎርጎራ የአካባቢውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ከፍ የሚያደርግ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ የባሕር ዳር ከተማን የኮሪደር ልማት ሥራ፣ አዲሱን የዓባይ ድልድይ፣ የጣና ዳርቻ አረንጓዴ ልማቶችን፣ የባሕር ዳርን ዓለም አቀፍ ስታዲየም እና ሌሎችንም የልማት ሥራዎች ተመልክተዋል።
“የባሕር ዳር ኮሪደር ልማት አልቆ ማሰብ ከተቻለ ባሕር ዳርን የበለጠ ውብ እና የአፍሪካ ምርጧ ከተማ ማድረግ እንደሚቻል ያሳየ ሥራ ነው” ሲሉም ተናግረዋል። መንገዶቹ ሰፍተዋል፣ ተውበዋል፤ ጣና ውበቱ ተገልጦ ለሕዝቡ ዕይታ ምቹ እና ማራኪ ኾኗል ብለዋል።
ባሕር ዳር እና አካባቢው ተፈጥሮ ውበት የቸረው ነው፤ ሐይቁ፣ አረንጓዴ ዛፎች፣ ኮረብታዎች እና ታላቁ የዓባይ ወንዝ ተሰናስለው የወለዱት ድንቅ ውበት አለ ብለዋል።
ይህ ውበት የሰው ልጅ እጆች፣ ጥበብ እና አስተውሎት ሲጨመርበት ደግሞ ምን ሊመስል እንደሚችል የኮሪደር ልማት ሥራው አሳይቶናል ብለዋል። አሁንም ቢኾን ተጨማሪ ሥራዎችን በማከናወን ተፈጥሮ የቸረችውን ውበት የበለጠ ማላቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።
“የልማት መሥኮት ተደጋግሞ ላይከፈት ይችላል፤ ለባሕር ዳር ከተማ የልማት መሥኮት ተከፍቶላታል፤ ይህንን እድል ተጠቅሞ ልማትን ማሳለጥ ይገባል” ሲሉም መክረዋል።
ልማቶች ሁሉ መሠረታቸው ማኅበረሰብ ነው፤ የባሕር ዳር አካባቢ ማኅበረሰብ ደግሞ የማደግ እና የመለወጥ ፍላጎት ያለው ሕዝብ ነው፤ በአልባሌ ነገር ሳይወሰድ በተጀመሩ የልማት ሥራዎች ላይ በብርታት መሳተፍ እና ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም በጣም ትልቅ ሥራ ነው፤ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ለማካሄድም በሚያስችል መልኩ እየተገነባ ነው ብለዋል።
ይኹን እንጂ ሥራውን በፍጥነት ማጠናቀቅ እና ለውድድር ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። በቀጣይ አሕጉራዊ ጨዋታዎችን በባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ለማዘጋጀት እየታሰበ ስለመኾኑም ገልጸዋል።
የእድገት ቁልፉ ልማት ነው፤ የልማት ደግሞ መደላድሉ ዕውቀት እና አስተውሎት ነው፤ የአማራ ክልል ሕዝብ ለሥራ ብርቱ እና እድገትን ውርሱ ለማድረግ የሚተጋ ሕዝብ ነው ብለዋል። ይህንን የቆየ ትልቅ እሴት ለመሸርሸር የሚጀማመሩ ነገሮች አልባሌ እንደኾኑም ጠቅሰዋል። በመኾኑም በአርቆ አስተዋይነት መቆም እና ሕዝብን እና ሀገርን በሚጠቅሙ ነገሮች ላይ ብቻ ጊዜን ማሳለፍ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

