ስዊድናዊው አጥቂ ቪክቶር ዮኬሬሽ ወደ አርሰናል የሚያደርገውን ዝውውር ለማጠናቀቅ በዚህ ሰዓት እንግሊዝ ለንደን መድረሱ ታውቋል።
ተጨዋቹ በነገው ዕለት የአርሰናል ዝውውሩን ለማጠናቀቅ የጤና ምርመራውን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። በተያያዘ ዜና የስፖርቲንግ ሊዝበኑ ፕሬዝዳንት ቫራንዳዝ ቪክቶር ዮኬሬሽ ልምምድ ባለመገኘቱ ምክንያት ቅጣት እንደጣሉበት ተገልጿል። ፕሬዝዳንቱ ቪክቶር ዮኬሬሽን የሐምሌ ወር ደሞዙን በቅጣት መልክ ማስከፈላቸውን የፖርቹጋል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ባየር ሙኒክ ሉዊስ ዲያዝን ለማስፈረም
የቡንደስሊጋው ክለብ ባየር ሙኒክ ኮሎምቢያዊውን ተጫዋች ሉዊስ ዲያዝ ለማስፈረም በድጋሜ ከሊቨርፑል ጋር ንግግር መጀመሩ ተገልጿል። ባየር ሙኒክ በቅርቡ ያቀረበው 58 ሚልዮን ፓውንድ የዝውውር ሒሳብ ውድቅ እንደሆነበት የሚታወስ ነው።
ባየር ሙኒክ አሁን ላይ የዝውውር ሒሳቡን አሻሽሎ አለማቅረቡን ዘ አትሌቲክ ዘግቧል። ሁለቱ ክለቦች በዝውውሩ ዙሪያ የሚያደርጉት ንግግር መቀጠሉ ተጠቁሟል። ኮሎምቢያዊው የፊት መስመር ተጨዋች ሉዊስ ዲያዝ በበኩሉ ሊቨርፑልን ለመልቀቅ ዝግጁ መሆኑ ተገልጿል።
ማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋቾቹን በርካሽ አይሸጥም
ሩበን አሞሪም ማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋቾቹን በርካሽ እንደማይሸጥ አጥብቆ ተናግሯል። ገዢ ክለቦች ለተጫዋቾቹ ክለቡ የሰጣቸውን ዋጋ ካልከፈሉ፣ አራቱን በገለልተኛነት ሲሰለጥኑ የቆዩ ተጫዋቾች ወደ ቡድኑ ለመመለስ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
አሌሃንድሮ ጋርናቾ፣ ጄደን ሳንቾ፣ አንቶኒ እና ታይሬል ማላሲያ ወደ አሜሪካ ከሚጓዘው የዩናይትድ ቡድን ውጪ የተደረጉ ሲሆን፣ ስለ መልቀቃቸው ንግግሮች እየቀጠሉ በመሆናቸው በካሪንግተን ከዋናው ቡድን ተነጥለው እየሰለጠኑ ነው።
“ቡድኑን የሚቀላቀሉበት ደረጃ ላይ ከደረስን፣ የእኛ ተጫዋቾች ስለሆኑ ቡድኑን ይቀላቀላሉ” ሲል አሞሪም ተናግሯል። “እነሱ (ገዢ ክለቦች) ያንን ዋጋ ካልከፈሉ፣ የማንቸስተር ዩናይትድ ተጫዋቾች ሆነው ይቀጥላሉ፣ በዚያ ላይ ምንም ጥርጥር የለኝም። ክለቦች የመጨረሻውን ደቂቃ እየጠበቁ እንደሆነ ተረድቻለሁ ነገር ግን ሊገረሙ ይችላሉ።”
ሊቨርፑል – ሁጎ ኢኪቲኬን አስፈረመ
ሊቨርፑል ሁጎ ኢኪቲኬን ከኢንትራ ፍራንክፈርት ማስፈረሙን ይፋ አድርጓል፡፡ የ23 ዓመቱ ፈረንሳዊ የፊት መስመር ተጫዋች በሊቨርፑል ለስድስት ዓመታት የሚያቆየውን ኮንትራት ተፈራርሟል፡፡ ሊቨርፑል ለተጫዋቹ ዝውውር 69 ሚሊየን ፓውንድ እና እየታየ የሚጨመር 10 ሚሊየን ፓውንድ በአጠቃላይ 79 ሚሊየን ፓውንድ ወጪ አድርጓል፡፡ ሁጎ ኢኪቲኬ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሁሉም ውድድሮች ለፍራንክፈርት 22 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን ÷ 12 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን ደግሞ አመቻችቶ አቀብሏል፡፡
ራሽፎርድ ባርሴሎናን ተቀላቀለ
የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ማርከስ ራሽፎርድን በውሰት ውል ከማንቼስተር ዩናይትድ አስፈርሟል፡፡ በዚህ መሰረትም ማርከስ ራሽፎርድ ለአንድ የውድድር ዓመት በውሰት ውል በባርሴሎና ቆይታ ይኖረዋል፡፡ ባርሴሎና በውሰት ውሉ ላይ የተቀመጠውን የመግዛት አማራጭ በመጠቀም ራሽፎርድን በቋሚነት ማስፈረም ይችላል፡፡
እንግሊዛዊው የፊት መስመር ተጫዋች ራሽፎርድ በባርሴሎና በሚኖረው ቆይታ 14 ቁጥር ማልያ እንደሚለብስም ተረጋግጧል፡፡ የ27 ዓመቱ ተጫዋች በ2024/25 የውድድር ዓመት ከጥር ወር ጀምሮ እስከ ውድደር ዘመኑ መጨረሻ ድረስ በውሰት ውል በአስቶንቪላ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ማርከስ ራሽፎርድ ባርሴሎናን መቀላቀሉን ተከትሎ ማንቼስተር ዩናይትድ በማህበራዊ ትስስር ገፁ መልካም ምኞቱን ገልጾለታል፡፡
አርሰናል ክሪስቲያን ሞስኬራን ማስፈረሙን ይፋ አደረገ
አርሰናል ወጣቱን ስፔናዊ ተከላካይ ክሪስቲያን ሞስኬራ ከቫሌንሲያ ማስፈረሙን ይፋ አድርጓል፡፡ የሰሜን ለንደኑ ክለብ ለ21 ዓመቱ ተጫዋች 13 ሚሊየን ፓውንድ መነሻ የዝውውር ሂሳብ ይከፍላል፡፡
ክሪስቲያን ሞስኬራ በመድፈኞቹ ቤት ለአምስት ዓመት የሚያቆየውን ውል የፈረመ ሲሆን፥ አርሰናል ተጫዋቹን ለተጨማሪ አንድ ዓመት ማቆየት የሚችልበት ማራጭ በውሉ ተካቷል፡፡

