የክረምቱ የዝውውር መስኮት ከተከፈተ ጀምሮ ስሙ በስፖርት አምዶች ያልተነሳበት ቀን አልነበረም፡፡ የ27 ዓመቱ ስዊድናዊ አጥቂ ቪክተር ጎከሬሽ በፖርቹጋሉ ክለብ ስፖርቲንግ በተለይ ባለፈው የውድድር ዓመት በግብ ፊት የማይሽኮረመም ድንቅ ተጫዋች መሆኑን አስመስክሯል፡፡
በተለይም መጪውን የውድድር ዓመት ሁነኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ በዝውውሩ የነቃ ተሳትፎ እያደረገ የሚገኘው የሚኬል አርቴታው አርሰናል ዐይኑን የነቀለበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡ ማንቼስተር ዩናይትዶች የግላቸው ሊያደርጉት አብዝተው ቢመኙም ጎከሬሽ ግን ምርጫው አርሰናል ብቻ ሆኗል፡፡
በስተመጨረሻም የሰሜን ለንደኑ ክለብ ንብረት ሆኗል፡፡፡ መድፈኞቹ አጥብቅው የተመኙትን ተጫዋች የግላቸው ማድረጋቸው ከተዘገበበት ቅስበት አንስቶ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የክለቡ ደጋፊዎች ደስታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
በአርሰናል ማለያ አንድም ጨዋታ ሳያደርግ፣ በኢምሬትስ የሚያሳየው ብቃት በውል ሳይታወቅ መድፈኞቹ ከወዲሁ ስለተደሰቱበት ምክንያት ጥያቄ የሚነሳ ከሆነ የስካይ ስፖርቱ አምደኛ ሳም ብሊዝ ያስነበበው ጽሁፍ መልስ አለው፡፡
ትውልዱ በስዊድኗ ዋና ከተማ ስቶክሆልም ነው፡፡ ኳስን ከእግሮቹ ያገናኘው ገና በ5 ዓመቱ እንደሆነ የሚነገርለት ተጫዋቹ በትልልቅ ክለቦች ተፈላጊ ለመሆን የበቃው እንዲህ በዋዛ አይደለም፡፡ በስቶክሆልም በሚገኘው ብሮማፖይካርና የወጣቶች ቡድን ባሳየው ተስፈኛ እንቅስቃሴ በ20 ዓመቱ በ1 ሚሊየን ዩሮ የእንግሊዙን ብራይተን መቀላቀል ችሏል፡፡
ሆኖም በቂ የመሰለፍ እድል ማግኘት ባለመቻሉ ወደ ስዋንሲ ሲቲ እና ወደ ጀርመኑ ሴንት ፓውሊ በውሰት ተሰጥቶ ተጫውቷል፡፡
ተጫዋቹ ለአሁን ተፈላጊነቱ ወሳኝ የሆነውን እንቅስቃሴ በማድረግ ራሱን ያሳየው የሻምፒዮንሺፑን ክለብ ኮቨንትሪ ሲቲ ከተቀላቀለ በኋላ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በኮቨንትሪ የሁለት አመት ቆይታው 40 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፥ 19 ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል፡፡
በሻምፒዮንሺፕ ባሳየው ብቃት ስፖርቲንግ በወቅቱ በክለቡ ታሪክ ውድ በሆነ 24 ሚሊየን ዩሮ ተጫዋቹን የግሉ ማድረግ ችሏል፡፡ በፖርቹጋሉ ክለብ ይበልጥ እየጎመራ የዘለቀው ተጫዋቹ በተቃራኒ ቡድን የግብ ክልል የሚታፈር ተጫዋች ለመሆን በቅቷል፡፡
ሳም ብሊዝ በጽሁፉ የአርሰናል ደጋፊዎች በተጫዋቹ መፈረም ከወዲሁ የመደሰታቸው ምክንያት ባለፉት ዓመታት ያስመለከተን ብቃትና ዘርፈ ብዙ ክህሎት ነው ይላል፡፡
ባለፈው የውድድር ዓመት ለፖርቹጋሉ ክለብ ስፖርቲንግ 39 ግቦችን ማስቆጠሩን በመጥቀስ በዚህም በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች የሚተካከለው እንደሌለ ያትታል፡፡
ከግብ አስቆጣሪነቱ ባሻገር በተለይም በአካላዊ ጥንካሬው፣ በማጥቃት ሽግግር ወቅት በሚያሳየው ቅልጥፍናና ፍጥነት፣ በግብ አጨራረስ፣ በኳስ ቁጥጥርና ተጫዋቾችን በማለፍ ክህሎቱ አሳማኝ እንቅስቃሴ ማድረጉን ይዘረዝራል፡፡
ነገር ግን በፖርቹጋል ሊግ ያሳየው ብቃት እንደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ባሉ ትልልቅ ሊጎች ላይ ለሚያሳየው ብቃት ትክክለኛ መመዘኛ ይሆናል የሚል መከራከሪያ መኖሩን ጠቅሷል፡፡ ለዚህም ኦፕታ ባለፈው ወር ባወጣው የእግር ኳስ ሊጎች ደረጃ የፖርቹጋል ፕሪሚየር ሊግ ከዓለም 8ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን አስታውሷል፡፡
ከፖርቹጋል ሊግ በብዙ ተደንቀው ወደ ፕሪሚየር ሊግ ከመጡ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የወቅቱ የሊቨርፑል አጥቂ ዳዊን ኑኔዝ ይጠቀሳል፡፡
በውድ የዝውውር ሂሳብ ከቤኔፊካ ወደ ሊቨርፑል የተዘዋወረው ኡራጋዊው አጥቂ በመጨረሻ ዓመት የቤኔፊካ ቆይታው 26 ግቦችን ማስቆጠር ችሎ እንደነበር ስካይ ስፖርት አስታውሷል፡፡
ነገር ግን በሊቨርፑል በቆየባቸው ሶስት ዓመታት ያን ያህል ግብ ማስቆጠር አልቻለም፡፡ ይህም ምናልባት ጎከሬሽ በበርካታ መመዘኛዎች ዐቅሙን ያስመሰከረ ተጫዋች ቢሆንም በተጠበቀው ልክ ውጤታማ ላይሆን ይችላል የሚሉ ወገኖች የሚያቀርቡት አንዱ መከራከሪያ ነው፡፡
ባለፉት ዓመታት እውነተኛ ዘጠኝ ቁጥር ማግኘት ላልቻለው አርሰናል የቪክተር ጎከሬሽ መምጣት ብዙ የሚለውጠው ነገር እንዳለም ሳም ብሊዝ ያነሳል፡፡
በ55 ነጥብ 1 ሚሊየን ፓውንድ እና ብቃቱ እየታየ የሚጨመር 8 ነጥብ 7 ሚሊየን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ ነው የአርሰናል ንብረት መሆኑ የተነገረው፡፡
የ27 ዓመቱ ተጫዋች በፕሪሚየር ሊጉ በቀድሞ አሰልጣኙ ሩበን አሞሪም የሚመራውን ማንቼስተር ዩናይትድ በመግጠም ሊጫወትለት ለጓጓው ክለብ ግልጋሎቱን እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡
በኃይለማርያም ተገኝ via fbc

