ከፓርቲነት ወደ “ቡድን” ስያሜ የተቀየረው የእነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድን (EFFORT) ትእምትን ልክ የትግራይ ክልልን እንደጠቀለለው አዲስ ቦርድ በርማቋቋምና የስራ አስኪያጅ ቅጥር በማውጣት የጀመረው እንቅስቃሴ ታገደ።
ይህንኑ ተከትሎ ድርጅቱን የሚመራው ቦርድ አካሄዱ ተቋሙን መቀመቅ ውስጥ የሚከት አደገኛና ህገወጥ አካሄደ መሆኑን ጠቅሶ ለክልሉ የፍትህ ቢሮ የእግድ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
በአቶ ቴድሮስ ሓጎስ የሚመራው የትእምት ባለ አደራ ቦርድ አመራር ” በትእምት (EFFORT) ስም የእነ ዶክተር ደረጽዮን ቡድን ያካሄዱት የምክር ቤት ጉባኤ ህገወጥ መሆኑን፣ ጉባኤው የመረጠው ኣብራሃም ተከስተ (ዶ/ር) የሚመራው ቦርድ በተቋሙ ላይ እያካሄደ የሚገኘው እንቅስቃሴም ህገወጥ በመሆኑ ተጣርቶ እግድ እንዲበየን ለፍትህ ቢሮ ጥያቄ ማቅረቡን ቲክቫኽ ያሰራጨው የትግርኛ የውሳኔ ደብዳቤ ያስረዳል።
በአንድ ወቅት ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃ ላይ እንደተቀመጠ በአቶ ስብሃት ነጋ የተመሰከረለትን ኤፈርት የተሰኘ የትህነግ የንግድ ተቋም በቀድሞ ቁመናው ላይ አይደለም። ይህ ሳያንሰው ህጋዊነቱን ያጣው የእነ ዶክተር ደብረጽዮን ቡድን ሊጠቀልለው ደፋ ቀና ማለቱን ተከትሎ የህጋዊ አካሄድ ችግር እንዳለበት ተጠቅሶ ክስ ከመቅረቡ በፊት ተቋሙን የሚመሩት ውገኖች አስጠንቅቀው ነበር።
” ካምፓኒዎቹን መቀመቅ የሚከት እብደት እንዲቆም የሚመለከተው አካል ሃላፊቱን ይወጣ ” ሲሉ የትእምት (EFFORT) ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ በየነ መክሩ “ላዛ ትግርኛ” ለተባለ የዩቱብ ሚድያ ቃለ መጠይቅ ሰጥተው ነበር።
በዚህም ” ህገወጥ ” ሲሉ የጠሩት የደብረፅን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ቡድን በትእምት ካምፓኒዎች ላይ ከፍተኛ አደጋ እንዲያንዣብብ እየተንቀሳቀሰ ነው በማለት ክስ ማሰማታቸውን ቲክቫህ ቀደም ሲል ዘግቦ ነበር።
” ዋና ስራ አስፈፃሚ ፣ ቦርድና የባለ አደራ ቦርድ በስራ እያለ ቡድኑ የራሱ ህገ-ወጥ ቦርድና የባለ አደራ ቦርድ በመሰየም ዋና ስራ አስፈፃሚ ለመቅጠር ማስታወቅያ በማስነገር ላይ ይገኛል” በማለት ነበር ክሳቸውን ያሰሙት።
አቶ በየነ ” ካምፓኒዎቹን መቀመቅ የሚከት ይህንን መሰል እብደት እንዲቆም የሚመለከተው አካል ሃላፊቱን ይወጣ ” የሚል ማስጠንቀቂያና ማሰሰቢያ አቅርበው ነበር።
“የቡድኑ ህገወጥ እንቅስቃሴ ካምፓኒዎቹ ከስራ ውጭ እንዳያደርግ ከጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደ (ሌ/ጀነራል) ተከታታይ ምክክሮች እያካሄድን ነው ” ያሉ ሲሆን ” ጉዳዩ በህግ-ማዕቀፍ እንዲታይ በክልሉ ፍትህ ቢሮ ክስ መመስርተናል ” ሲሉ የተከተሉትን አካሄድና የህግ መስመር አመላክተው ነበር።
“ይህን ሳይሳካ ከቀረ ግን የፌደራል መንግስት በትእምት ካምፓኒዎች ላይ በጦርነቱ ጊዜ ያስቀመጠው እግድ መልሶ ለማየት የሚገደድበት ሁኔታ ዝግ አይደለም” የሚል ማሳሰቢያም አስከትለው ነበር።
” ነባሩ ቦርድ ህጋዊ ነው ፤ በትእምት ስም የተካሄደው የምክር ቤት ጉባኤ ህጋዊ አይደለም ” የሚል ውሳኔ የተሰማው ከላይ በተገለጸው አግባብ መሰረት ህጋዊ የዕግድ ጥያቄ ከቀረበ በሁዋላ ነው።
ቲክቫህ ከመቀለ እንዳገኘው ጠቅሶ ባሰራጨው መረጃ መሰረት ነባሩ የትእምት ኢንቨስትመንት አመራር ” ህገወጥ የምክር ጉባኤ አካሂዶ ህግን ያልተከተሉ አመራሮች መርጦ በተቋሙ ላይ የጀመረው ህገወጥ እንቅስቃሴ ይታገድልኝ ” ሲል ለክልሉ የፍትህ ቢሮ ያቀረበው ክስ ተቀባይነት አግኝቷል።
በአቶ ቴድሮስ ሓጎስ የሚመራው የትእምት ባለ አደራ ቦርድ አመራር ” በትእምት ስም የተካሄደው የምክር ቤት ጉባኤ ህገወጥ ነው ፤ በጉባኤው የተመረጠ በኣብራሃም ተከስተ (ዶ/ር) የሚመራ ቦርድ በተቋሙ ላይ እያካሄደ የሚገኘው እንቅስቃሴም ህገወጥ መሆኑ ተጣርቶ ይታገድልኝ ” ሲል ለፍትህ ቢሮ አቤታቱ አቅርቧል።
ሦስት አጣሪ አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም ላለፉት 10 ቀናት የቀረበለት አቤቱታ ሲመረምር የቆየው የፍትህ ቢሮ ” በኣብራሃም ተከስተ (ዶ/ር) የሚመራ ቦርድ ህጋዊ አይደለም ” በማለት በትእምት ላይ የሚያደርገው እንቅስቃሴ እንዲያቆም የእግድ ውሳኔ ሰጥቷል።
” የትእምት ምክር ቤት ባለፈው የካቲት 2017 ዓ.ም ባካሄደው ጉባኤ መርጦኛል ” በሚል በመንቀሳቀስ ላይ ያለውና የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ በየነ መክሩ ህጋዊ ርክክብ ባላካሄዱበት ሁኔታ በላያቸው ላይ አዲስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ለመቅጠር በሚድያዎች እስከማስነገር የደረሰው በኣብራሃም ተከስተ (ዶ/ር) የሚመራው አካል ” ህጋዊ አይደለህም ” የሚል የፍትህ ቢሮ ውሳኔ ያከብር ይሆን ? የብዙዎች ጥያቄ መሆኑ እየተደመጠ ነው።
ባለፈው መጋቢት 2017 ዓ.ም በተፈጠረው የፓለቲካ ቀውስ ምክንያት የቀድሞ ፕሬዜዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከትግራይ መውጣታቸው ተከትሎ የትእምት ኢንቨስትመንት ዋና ስራ አስፈፃሚና የባለ አደራ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ በየነ መክሩና አቶ ቴድሮስ ሓጎስ ከክልሉ ውጪ ናቸው።
የትእምት ዋና ስራ ስፈፃሚ በየነ መክሩ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ላዛ ትግርኛ ለተባለው ሚድያ ከአዲስ አበባ በሰጡት ቃለመጠይቅ ” ህገወጥ ቡድኑ በሃይል ካስቀመጣቸው አመራሮች የተደረገ ርክክብ የለም ፤ ዋና ስራ አስፈፃሚና ቦርድ የነበረው ነው ያለው ነው ” ማለታቸው ቲክቫህ የዕግድ ውሳኔውን ሲዘግብ አስታውሷል። አያይዞም የትህነግ ትልቁ የንግድ ኢምፓየር አሁን ላይ የሚገኝበትን ቁመናም በነጥብ ለይቶ አስቀምጧል።
- የትእምት 60 በመቶ ሃብት በጦርነቱ ወድሟል ፤ መሰቦ ስሚንቶ ፋብሪካ አርጅቷል ፤ ትራንስ ኢትዮጵያ ከነበሩት 500 መኪኖች አሮጌ 100 መኪኖች ብቻ ነው የቀሩት ፤ አልመዳ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በአውሮፕላን ቦንብ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል። “
- ” የፌደራል መንግስት ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 ዓ.ም በትእምት ካምፓኒዎች ላይ አኖሮት የነበረው እግድ ለጊዜው ሲያነሳ ካምፓኒዎቹ ከህወሓት ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው መስራት እንዳለባቸው ቅድመ ማስጠንቀቂያ ስጥቶ ነው ያስረከበን ”
- ” የፌደራል መንግስት በትእምት ካምፓኒዎች ያስቀመጠው እግድ ሙሉ በሙሉ ባለነሳበት ሁኔታ ሆነን ከፓለቲካ ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው እንዲያንሰራሩ ስንሰራ ነበር፤ ህገወጡ የህወሓት ቡድን ከካምፓኒዎቹ ላይ እጁ የማያነሳ ከሆነ የፌደራል መንግስት እግድ ሊቀጥል ይችላል። “
- በተጨማሪም በሻዕቦያ አማካይነት ከፍተኛ ዝርፊያ የተፈጸመበት፣ የመገልገያ መሳሪያዎቹና፣ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የመቆፈሪያ ማሽኖች እንዲሁም ማምረቻዎችን ከበርካታ መለዋወጫዎች ማጣቱ በጦርነቱ ወቅት በዝርዝ ሲቀርብ ነበር።
ትእምት ኢንቨስትመንት በስሩ አስራ አምስት ግዙፍ ካምፓኒዎች ይካተተና የፓርቲ ንብረት የነበረ፣ በስልታን ላይ በነበረው ትህነግ አማካይነት የተበላሸ በሚል ከፍተኛ ሃብት ብብድር የወሰደ፣ በሚፈለግበት ደረጃ ቀረጥ የማይከፍል፣ የአቻ ፖለቲካ ድርጅት የንግድ ኢንዶውመንቶችን የዋጠ፣ ቀረጥ ሳይከፍል ያሻውን ምርት ከውጭ የሚያስገባ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ በአፍሪካ ማዕድን ዘርፍ ላይ መሰማራቱን አቶ ስብሃት የመስከሩለት፣ በውጭ አገራት ሪለስቴቶች ያሉት ግዙፍ የንግድ ኢምፓየር እንደነበር አይዘነጋም።

