የጉምሩክ ኮሚሽን ከ40 ቀናት ክትትል በኋላ ግምቱ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ 27.75 ኪሎ ግራም ጥፍጥፍ ወርቅ በቁጥጥር ስር አውሏል። ፖሊስ ይፋ ባያደርገውም የውጭ አገር ዜጎች አሉበት።
የጉምሩክ ሕግ ተገዥነት ዘርፍ ም/ኮሚሽነር አዝዘው ጫኔ በተለይም ለኢቢሲ ዶትስትሪም እንደገለፁት፤ ጥፍጥፍ ወርቁ በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር በአዲስ አበባ ከተማ በቃሊቲ ጉምሩክ ቅርንጫፍ በቱሉዲምቱ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ዓርብ ሌሊት አስር ሰዓት አካባቢ ተይዟል።

በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የተያዘው ወርቅ በአውቶሞቢል አካል ውስጥ ደብቀው ሲያዘዋውሩ ከነበሩ 3 ተጠርጣሪዎች እና ሁለት ተሽከርካሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ብለዋል፡፡
ሕገወጥ የወርቅ አዘዋዋሪዎቹ ላይ ለ40 ቀናት ያህል ከፍተኛ ክትትል ሲደረግበት ቆይቶ ከምሽቱ 10 ሰዓት በጉምሩክ የኢንተለጀንስ ባለሙያዎች መያዙን አስታውቀዋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎቹ በተጨማሪ ሌሎች ሊጣሩ የሚገባቸው መረጃዎችም መያዛቸውንና ጉዳያቸውም ለፍርድ ለማቅረብ የምርመራ ሥራ እየተሰራ መሆኑን አቶ አዝዘው ተናግረዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኢንተለጀንስ ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር ያዋሉት ወርቅ ዛሬ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉንም አቶ አዝዘው ተናግረዋል።
የኮንትሮባንድ እና ሕገወጥ ንግድ ድርጊቶችን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመከላከል ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ኀብረተሰቡ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከመከላከያ፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነትና ከክልል የህግ አስከባሪ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ኮንትሮባንድን ለመከላከል እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

