የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ ለጋዜጣ ፕላስ እንደገለጹት፤ በሰው የመነገድና በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና የብዙ የሰዎች ህይወት እየቀጠፈ ያለ ወንጀል ነው፡፡
በወንጀሉ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ወንጀለኞች በአዋጅ ቁጥር አንድ ሺህ 178 መሰረት የሞት ቅጣት፣ የዕድሜ ልክ እስራትና እስከ 25 ዓመት እስራት ያስቀጣል ብለዋል፡፡
በመሆኑም በ2017 በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በሂደቱ የተሳተፉ 5 ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ እንዲወስን መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
በሰው የመነገድ ወንጀል ለመከከላከልና ለመቆጣጠርም የግንዛቤ ማስጨበጫ እና በክልሎች መካከል ቅንጅትና ትብብር የሚፈጥሩ ስራዎችና መመሪያ የማጽደቅ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም በህገወጥ ድርጊቱ በስፋት ተጠቂ ለሆኑት ወጣቶች በሀገር ወስጥ የስራ እድል ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ሰው የመነገድና በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልም ድንበር ተሻጋሪ የተደራጀ ወንጀል መሆኑን አንስተው፤ ይህንንም ለመቆጣጠር ከጅቡቲ፣ ኬንያና ማላዊ ጋር ዓለም አቀፍ ትብበር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ባለፈው በጀት ዓመት የተወሰደው የህግ እርምጃ እንደሀገር የተሰጠውን ትኩረት ማሳያ ነው፡፡
በቀጣይም የተሻለ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተጠናክሮ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

