ከአንድ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ድርጅት ጋር በመተባበር ልዩ ልዩ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ይዘን ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረን ነበር፡፡ ወልቂጤ፣ ጅማ፣ አርባ ምንጭ፣ ሐረር፣ ደሴና መቀሌ ሄደናል፡፡ ሁሉም በሰላም ተጠናቋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ባህር ዳር፣ ጎንደርና ሁመራ ሄደን ነበር፡፡ ባህር ዳር ላይ የተደራጁ ጫኝና አውራጆች መኪናዎቻችንን ከወረሩ በኋላ ኃይለ ቃል በተሞላበት ንግግር እያመናጨቁን፣ ከእኛ ውጪ ማንም ሊያወርድ አይችልም፣ መክፈል ያለባችሁም ለእያንዳንዱ ካርቶን 50 ብር ነው ይሉናል፡፡
የተጫነው በድጋፍ የመጣ የትምህርት ቤቶች መርጃ መሣሪያ እንደሆነ፣ መክፈል ያለብንም ከ20 ብር ሊበልጥ እንደማይችል ብንነግራቸው የሚሰሙ አልሆኑም፡፡ መጨረሻ ላይ 30 ይሁንላችሁ ብንላቸውም እምቢ ይሉናል፡፡ ክርክሩ እየተካረረ በመሄዱ ምክንያት ችግር እንዳይፈጠር በመፍራት ለከተማ አስተዳደሩ ስልክ በደወልንበት ቅጽበት አስተዳደሩ የጸጥታ ኃይል ልኮ ችግር ፈጣሪዎችን አባሮ ሌሎች ሠራተኞችን አምጥቶልን ችግሩ ሊፈታ ችሏል፡፡ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምስጋና ይግባው፡፡
ትልቅ ፈተና የገጠመን ጎንደር ከተማና ከጎንደር ከተማ እስከ ሶሮቃ ባለው መስመር ላይ ነው፡፡ ጎንደር ከተማ ከብዙ ጊዜ ጀምሮ የጫኝና አውራጅ አምባገነንነት የሰፈነባት ከተማ ሆና ቆይታለች፡፡ የጎንደር ከተማ ጫኝና አውራጅ የለየለት ወንበዴና የኢንቨስትመንት ፀር ነው፡፡ ንግግራቸው የጎንደርን እሴት የማይመጥን፣ ሁሉን ነገር በጉልበት ለማስፈፀም የሚሞክሩ፣ የመጫኛና ማውረጃ ዋጋውን ከልክ በላይ ቆልለው እኛ ያልነው ካልሆነ ምንም ነገር ማንቀሳቀስ አይቻልም የሚሉ ወንበዴዎች ናቸው፡፡ ተከታታይ የከተማ አስተዳደሩ መሪዎች ሊስተካክሉት ያልቻሉት ይህ ኀይል ለትምህርት ቤቶች በእርዳታ የሄደን ንብረት አግቶ በመያዝ ብዙ አንገላቶናል፡፡ የተከፈለው ገንዘብም እጅግ ብዙ ነው፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደር የጫኝና አውራጅን የተደራጀ ውንብድና በፍጥነት መልክ ካላስያዘ በከተማው እንኳን አዳዲስ ኢንቨስትመንት ሊመጣ ያለውም መቀንጨሩ የማይቀር ነው፡፡ ይህን ማስተካከል ከባድ ሊሆን አይገባም።
ከጎንደር ከተማ ወጥተን እስከ ሶሮቃ በተጓዝንበት መንገድ የገጠመን ደግሞ “የሽፍታ አምባገነንነት” ሊባል የሚችል ነው፡፡ የተደራጁ ሽፍታዎች (እነሱ ፋኖ ነን ይላሉ) ከ9 ጊዜ በላይ እያስቆሙ ብዙ አንገላተውናል፡፡ ለሕይወታችን አስጊ የሆነ ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር፡፡ በቆምንባቸው ሁሉም ቦታዎች የያዝነው ቁሳቁስ ምን እንደሆነ እያሳየናቸውና ለማን እንደሆነ እየነገርናቸው፣ ፈፅሞ ግድ ሳይሰጣቸው ገንዘብ እንድንከፍል አድርገውናል፡፡ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያለው “የነጻነት ታጋይ” ምን የሚሉት ነው?
በአማራ ክልል ለሁለት ተከታታይ ዓመታት ከ7 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ ሆነው ቆይተዋል፡፡ የተሰደዱና የተገደሉ መምህራን በጣም ብዙ ናቸው፡፡ የተሰደዱና ያለ እድሜያቸው እንዲያገቡ እየተደረጉ ያሉት ተማሪዎችም በርካታ ናቸው፡፡ ይህ አደገኛ ሁኔታ በመጪው ዓመትም የሚቀጥል ከሆነ የዘመናት ስብራትን መፍጠሩ አያከራክርም፡፡
በመጪው መስከረም ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ከሁሉም አካላት የተባበረ ሥራ ይጠበቃል፡፡ በትምህርት መስክ የተሰበረ ኅብረተሰብ በየትኛውም መስክ ሊሳካለት አይችልም!
Via Berhiun adane ነጻ አስተያየት

