የአፍሪካ ዋና ከተማነትን ከአዲስ አበባ ወደ ሌላ ከተማ እንዲቀየር በበታችነት ስሜት የሚሰቃዩት የኤርትራ ሰዎች መጠየቃቸው ተሰምቷል። ዜናውን የሰሙ ” ወደ አሰመራ ነው የሚዘዋወረው” ሲሉ ስላቅ ተጫውተዋል። አሳቡ የተለመደው የቅናትና የበታችነት ስሜት የወለደው መሆኑንም አመልክተዋል።

የአፍሪካ ህብረት (AU) ዋና መስሪያ ቤት ከአዲስ አበባ እንዲነሳ የኤርትራ ሰዎች መጠየቃቸው ሟቹ የሊቢያው መሪ ከሞከሩት ሙከራ ጋር የተገናኘ፣ ጭልጥ ያለ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነውን የኤርትራ መሪ ማንነትና አጀንዳ በግልጽ ያሳየ አንድ ጉዳይ ሆኗል።
በብሄርና በሻዕቢያ አጀንዳ ተጠምቀው “ኢሳያስ ለኢትዮጵያ ቅን አሳቢ ናቸው” በማለት የሚሰብኩት “ኢትይጵያ ነን” ባይ የማህበራዊ ሚዲያ ስር ታጋዮች ዜናውን በዝምታ አልፈውታል። ይህ ዜና በይፋ እየተሰራጨ ያለምንም ይሉኝታ ለኢትዮጵያ እየሰሩ ያሉ ዜጎችንና መሪዎችን ነጥለው በማውገዝ ከኢሳያስ ሊያሳንሱዋቸው የሌት ተቀን ስራቸውን ገፍተውበታል።
በቅርቡ የአፍሪካ ህብረት (AU) ዋና መስሪያ ቤትን ከአዲስ አበባ እንዲዛወር የሚጠይቅ አቤቱታ መቅረቡን ተከትሎ፣ በሆርን ሪቪው ተመራማሪ በሆኑት በቤተልሔም ፍቅሩ የቀረበ መረጃ ላይ የተመሰረተ ትንታኔ፣ ይህ ጥያቄ በሁለት አመክንዮ ላይ የተመሰረተና የፓን-አፍሪካኒዝምን ታሪካዊ እና መንፈሳዊ መሰረት የሚክድ መሆኑን አመልክተዋል። ጸሐፊዋ፣ ይህ አቤቱታ ከኤርትራ ጋር የቅርብ ግንኙነት ባላቸው ግለሰቦች የቀረበ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ጸሃፊዋ አዲስ አበባ የአፍሪካ መቀመጫ እንድትሆን ያደረጋት ምርጫ ድንገተኛ ሳይሆን የአፍሪካን የነጻነት እና የራስን የመወሰን ፍላጎት ያረጋገጠ ታላቅ ታሪካዊ ውሳኔ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተያዘች ብቸኛ የአፍሪካ ሀገር እንደመሆኗ፣ በአፍሪካ የነጻነት ንቅናቄዎች ውስጥ የማይናወጥ የሉዓላዊነት ምንጭ ሆና ማገልገሏ በዚሁ ጽሁፍ ተመልክቷል። “በጣሊያን ተገዝተናል” በሚል ባርነትን ጌጥ ላደረጉና የኩራት ተምሳሌት ላደረጉ ባንዶች ባይገባቸውም አፍሪካ በዚህ የደመቀ የኢትዮጵያ ታሪክ እጅግ እንደምትኮራ በተደጋጋሚ መገለጹ የሚታወስ ነው።
ቤተልሔም፣ ይህንን ታሪካዊ ምሳሌያዊነት “ጊዜው ያለፈበት” ብሎ መፈረጅ፣ የፓን-አፍሪካኒዝምን መሰረታዊ መነሻ እንደ መካድ ይቆጠራል ሲሉ ታሪክን በተለይም አፍሪካን አንድ ያደረገውን አብረቅራቂ ድል ለማመለከት ሞክረዋል።
ጸሐፊዋ፣ የአፍሪካ ህብረትን ከአዲስ አበባ የማዛወር ሙከራ፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ፣ ምሳሌያዊ እና ተግባራዊ ሚና ለመናድ የሚደረግ ሳይንሳዊ ያልሆነ ጥረት ነው ብለዋል።
“ኢትዮጵያ አስተናጋጅ ብቻ ሳትሆን፣ የአፍሪካ ህብረት ጥልቅ መንፈሳዊ እና ታሪካዊ መኖሪያ ናት” በማለት መንፈሳዊ ትርጉሙን በማስረዳት አሳባቸውን ቋጭተዋል።
“ሻዕቢያ የአፍሪካ ሕዝብረት ከአዲስ አበባ ይነሳ ካለ አይቀር የዚህ ዘመን ገዳም፣ ጨለማና ሰዓት የቆመባት አገር ወደምትባለው አገራቸው እንዲዛወር በገሃድ አክለው ቢጠይቁ ጥሩ ነበር። ስላቁንም ሙሉ ያደርገው ነበር” ሲሉ ምርጫ፣ ካቢኔ፣ ሕገመንግስት፣ ፕሬስ፣ ፓርቲ፣ ኢንተርኔት፣ ኤቲኤም፣ ኢንተርኔት፣ መንገድ፣ ሆቴል፣ መብራት፣ በጀት ወዘተ ህልም ለሆነባት አገር የሚሆን ራዕይ ትወደርጎ በታሪክም ይመዘገብ እንደነበር አመልክተዋል።

