የአባይ ወንዝ መገደብ የግብጽንም ሆነ የሱዳንን የውሃ ድርሻ ቅንጣት አላጓደለም። ኢትዮጵያ የሁለቱንም አገሮች የወሃ ፋልጎት ማስተጓጎል እንደማትፈልግ በተደጋጋሚ ብታስታውቅም ግብጽ እሪታዋን ማቆም አልፈለገችም። ውሃ ከልተጓደለ ግብጽን በዚህ ደረጃ አሳብዶ ኢትዮጵያን ዙሪያዋን በመክበብና በሻዕቢያ በኩል ባንዶችን በማደራጀት ትርምስ ለመፍጠር መትጋቷ ለምን ይሆን የሚል ጥያቄ የሚሊዮኖች፣ ጉዳዩን በድርድር ለመፍታት ለሚሞክሩ አካላት ጥያቄያቸው ነበር።
“የአባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ተራሮች አጥቦ ይወስድ የነበረው አረራችንን ብቻ ሳይሆን ወርቃችንንም ነው” ሲሉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው የግብጽን ያላሰ፤እሰ ጩኸት መነሻና መዳረሻ ያሳየ ሆኗል። በዚህም ሳቢያ ዜጎች ጉዳዩን በስፋት መነጋገሪያ አድርገውታል። የቁጭት መነፍስም ፈጥሯል።
ጠ/ሚኒስትሩ በሀገሪቱ የመንግስት እና የህዝብ መገናኛ ብዙሃን በተላለፈው ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዘ ገለጻቸው፤ ግድቡ መገንባቱን ተከትሎ “የተከማቸውን ደለል ስናስፈትሽ ወርቅ እያገኘንበት ነው” ሲሉ ተድምጠዋል። “ለካስ አባይ አፈር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ወርቅ ነው ከተራሮቻችን ላይ አጥቦ ሲወስድ የነበረው የሚል ተጨማሪ ቁጭት እንዲፈጠር ያደርጋል” በማለት የአባይን ሳይገደብ መኖር የሚፈጥረውን ቁጭት አመላክተዋል።
“ለእኛ የሚገባንን ማጓደልም ሆነ፤ ሌሎች የሚገባቸውን ማስቅረት ፍትህ ማዛባት ነው። የሚገባንን በተገቢው መንገድ ተጠቅመን ለሌሎች የሚገባቸውን ማድርግ ግን ፍትህ ነው”
“አፈራችን፣ ወርቃችን፣ አሳዎቻችን፣ ግንዶቻችን፣ ዛፎቻችን ተወስደው አንድም ሰው ኑሩልን፣ እድሜያችሁ ይርዘም፣ ከናንተ የተነሳ ይሄንን አገኘን ሲባል ሰምቼ አላውቅም” በሚል ኢትዮጵያ ባጎረሰች እጇን የተነከሳች አገር መሆኗንም ገልጸዋል።
“ወደብ እንድናጣ የተደረግንበት አግባብ ያሳዝነኛል ይቆጨኛል” በማለት ኢትዮጵያ የታነቀች አገር መሆኗ በሃዘኔታ ሲገልጹ ካሳዩት ስሜት በተቃራኒ ” አባይ ተገንብቶ ተጠናቆ ማየቴ እጅግ ኩራት ይሰማኛል። ፈጣሪን አመሰግናለሁ” ሲሉ የተደመጡት አብይ አህመድ፣ አባይ ተገደበ ማለት ብዙ የችግር ቀዳዳዎች ተደፈኑ እንደማለት መሆኑን አስረድተዋል።
“ሀብታችሁን ትከላከላላችሁ፣ ትጠብቃላችሁ የሚል ቁጣና ተግሳጽ ነው የሰማነው” የሚል ክስ ቀደም ሲል ጀመሮ ሲቀርብ እንደነበር ያስታወሱት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በንድፍና በፕሮጀክት ደረጃ አስቀድሞ የነበረውን ግድብ የመስራት ሕልም አቶ መለስ በማስጀመራቸው ምስጋና እንደሚገባቸው፣ አቶ ኃይለውማሪያም ደሳለኝም በተመሳሳይ ምስጋና እንደሚገባቸው አመልክተው ነበር።
ከማህበራዊ ጉዳይ አማካሪያቸው ዲያቆን ዳንዔል ክብረት ጋር እዚያ እግድቡ ከንፈር ላይ ተቀምጠው ባደረጉት ቃለ ምልልስ አብይ አህመድ እሳቸው ወደ ኃላፊነት እንደመጡ ፕሮጀክቱን ሲጎበኙ የፈራረሰ ከተማ ይመስል እንደነበር አስታወሰዋል። በዚህም ሳቢያ ፕሮጀክቱ ተከልሶ ዳግም በማስተካከል ለመስራት ተጨማሪ ወጪና ጊዜ መውሰዱን አመልክተዋል። እሳቸው ባይናገሩትም ግድቡ በተባለው ጊዜ ጥንቅቅ ተደርጎ ቢሰራ ኖሮ ዛሬ ላይ የወታበትን መመለስና ሌሎች ግድቦችን ለመስራት በተቻለ ነበር በሚል ስሌት አስልተው ቁጭታቸውን የገለጹ በርካቶች ናቸው።
ከቀናት በኋላ በይፋ ይመረቃል ተብሎ የሚጠበቀው የህዳሴ ግድበ መገንባት “ለጎረቤት ሀገራት እንኳን ውሃ ሊያስቀርባቸው በዝቶ እየሄደላቸው ነው፣ ደለል ሁኖ የሚያስቸግራቸውን አፈር አስቀርቶላቸዋል” ሲሉ አስተባብለዋል።
አንዳንዶቹ “ውኃው ወደታች እንዳይፈስ ገድቡት፤ አስቀሩት” የሚሉ አሉ ሲሉ ጠቁመው፤ “ይህ ግን የእኛ ፍላጎት አይደለም፤ ውኃውን ሙሉ በሙሉ መገደብም አይቻልም” ብለዋል።
አሁን ላይ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ 74 ቢሊዮን ሜትር ኪዩቢክ ወይም 74 ትሪሊየን ሊትር ውኃ መያዙንም አስታውቀዋል። ይህን ይዘንም በአሁኑ ወቅት ውኃ በተርባይን ብቻ ሳይሆን በማስተንፈሻውም ጭምር እየወጣ ነው፤ ከታሰበው በላይ ውኃ የመያዝ ፍላጎት የለንም፤ እንያዝ ብንልም ግድቡ አይችልም ሲሉ አስረድተዋል።
“እኛ ስንከሰስ የኖርነው የሰው እንደወሰድን እንጂ፤ የሚገባንን በጣም በጥቂቱ መጠቀም እንደጀመርን አይደለም ሲሉ” ተደምጠዋል። በተጨማሪም ጠ/ሚኒስትር አብይ በገለጻቸው ህዳሴ ግድብ ከኢነርጂ ምርት ባለፈ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አመልክተዋል።
ከግድቡ በየአመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ለግድቡ የወጣውን ወጪ በተወሰኑ አመታት ውስጥ እንደሚመልስ ተናግረዋል።
በታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ያለው ሐይቅ ስም “ንጋት” እንዲባል መወሰኑን ጠ/ ሚኒስትር አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ገዙፉን የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአፍሪካውያን ራስን የመቻል እና የአከባቢያዊ ልማት ተምሳሌት መሆኑን በቅርቡ ገልጻለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፣ “የግድቡ መጠናቀቅ የአፍሪካውያን ራስን መቻልና አከባቢያዊ ልማት ተምሳሌት ነው” ብለዋል።
ግብፅ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ከምትከተለው ፖሊሲ ጋር የሚጻረር አዲስ የዲፕሎማሲያዊ ቅስቀሳ እና የማግባባት ስራ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ላይ መጀመሯ ተዘግቧል።
የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ትናንት ሐሙስ ዕለት ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከጅቡቲ፣ ከዩጋንዳ፣ ከኬንያ እና ከሶማሊያ አቻዎቻቸው ጋር በስልክ መነጋገራቸውን የግብጽ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ሚኒስትሩ በንግግራቸውም “በናይል ተፋሰስ ላይ ዓለም አቀፍ ህግን የሚጥሱ የአንድ ወገን እርምጃዎችን ግብፅ ውድቅ ማድረጓን በድጋሚ አረጋግጠዋል” ሲል የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቅርቡ ይመረቃል መባሉን ተከትሎ “ግብፅ እክል ለመፍጠር እየተሯሯጠች ነው” ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢ/ር አሸብር ባልቻ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ከሰዋል። አክለውም “የሚቀየር ነገር የለም፤ ያለቀ እና የሞተ ጉዳይ ተደርጎ ነው መወሰድ ያለበት” ብለዋል።

