ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነዋሪነቱ ከኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች በአንዱ ያደረገና ለጊዜው በስም ባልገለጸው አንድ ሚዲያ ይሰራ የነበረ ሪፖርተር ገቢው መንጠፉን ለባልደረቦቹ ሲያስረዳ ” ዩኤስ አይዲ መዘጋቱ እርዳታ ሲሰጣቸው የነበሩትን ሚዲያዎች ኪስ በማድረቁ ገቢዬ ቆሟል” ማለቱ ተሰምቷል። እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በተመሳሳይ አገር ቤት ሆነው በእነዚሁ ተደጓሚ ሚዲያዎች ውስጥ በግልጽና በድብቅ ሲሰሩ የነበሩ ተቀንሰዋል። ላመጡት መረጃ ይከፈላቸው የነበሩ ግንኙነታቸው ተበጥሷል።
“አዲስ አበባ ካለው ቢሮ በእኔ ስር ሲሰሩ የነበሩ ሶስት ሪፖርተሮች በገንዘብ እጥረት ተባረዋል” የሚለው የዛሬው የጎረቤት አገር ነዋሪ ለዝግጅት ክፍላችን ተባባሪ እንዳለው መረጃ ያቀብሉ የነበሩም ግንኙነታቸው ተቋርጧል።
የመንግስት ሚዲያዎች ውስጥ ከሚሰሩ የሚዲይሳ ሰዎች በክፍያ በድብቅ ዜናና የውስጥ ደብዳቤዎች ያገኙ እንደነበር የሚናገረውና አሁን ላይ በሩዋንዳ የሚኖረው ሌላው “ጋዜጠኛ ” እንዳለው አሁን ላይ ሁሉም በሚባል ደረጃ መረጃ መሸጥ አቁመዋል። ምክንያቱ ደግሞ ከዩኤስ አይዲ መዘጋት ጋር ተያይዞ ሚዲያዎቹ ኪሳቸው በመራቆቱ ነው።
“በመንግስት ሚዲያ ውስጥ በክፍያ መረጃ ማግኘት የተለመደ ነው” የሚለው የሩዋንዳው ነዋሪ አሁን ላይ ጠብመንጃ ያነሱ የብሄር ድርጅቶችና እነሱን በሚያስተባብሩት በኩል በሚረዱት ሚዲያዎች በአንዱ ይሰራል።
ለዝግጅት ክፋላችን ቅርብ የሆኑና ይህን መረጃ በስፍራው በማሰባሰብ የላኩልን እንዳሉት፣ መረጃ የሰጡዋቸው አካላት እንዳሉት በስፋት መረጃ በማግኘት ይታወቁ የነበሩት ሚዲያዎች አሁን ላይ እንደ ቀድሞው ጥሬ መረጃ አያገኑም። ምክንያቱም ከላይ የተገለጸው ነው።
“ዩኤስ አይዲ በመዘጋቱ በድብቅ እየከፈሉ መረጃ የሚያገኙ ሚዲያዎች ወሬ እያጡ ነው” በማለት ያስታወቀው ዩጋንዳ በስደት የሚኖረው ሪፖርተር አሁን ላይ ቡና በመሸጥ እንደሚተዳደር ይናገራል። ምን አልባትም ወደ አገሩ ሊመለስ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል።
በሩዋንዳ የሚገኙ የተለያዩ የዩቲዩብ ሰራተኞች፣ በኢትዮጵያ የብሄር ብጥብጥን ስፖንሰር በሚያደርጉ የሚታወቁ አገሮችና ተባባሪዎቻቸው እንደሚደጎሙ ያስታወቀው የሩዋንዳው ነዋሪ፣ ኬንያ ብዙ ምቾት ስለማይሰጥ ወደ ሩዋንዳ ማምራታቸውን መናገሩን መረጃውን ከላኩት ወገኖች ለመረዳት ተችሏል። ያም ሆኖ ኬንያ ውስጥም ሆነው የሚሰሩ እንዳሉም አክለው ገልጸዋል።
“ይናበባሉ” የሚሉት የሚዲያዎቹን አሰራር የሚከታተሉ ወገኖች፣ አዲስ አበባ ሆነው ለነዚሁ ሚዲያዎች መረጃ የሚሸጡት የመንግስት ሰራተኞች ስጋት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
” እኔ የምሰራበት ሚዲያ / ስሙ ለጊዜው ያልተገለጸ/ ሶስት ሰራተኞቹን ካባረረ በሁዋላ ድጋፍ በማጣቱ አሁን ላይ መረጃ አልባ ሆኗል። በፊት ከሚታወቅበት አግባብ አንጻር አሁን ላይ ባዶ ነው ማለት ይቻላል” ያለው የጎረቤት አገር ነዋሪ፣ ኤሊያስ መሰረት በፋክት ቼክ ብቻ ዳጎስ ያለ ጥቅም ያገኝ እንደነበር አመልክቷል።
ይኸው ምስክር ድጎማው ሲቆም እንደ ሌሎቹ ስማቸው ያልተጠቀሰ ነገር ግን የሚታወቁ ሚዲያዎች፣ ኤሊያስ መሰረትም በተመሳሳይ ያሰራቸው የነበረውን ሰራተኞቹን ማሰናበቱን ያወሳው ምስክር፣ በገንዘብ ችግር ሳቢያ መስራት የማይችልበት ደረጃ ደርሶ እንደነበር በራሱ የፌስ ቡክ ገጹ ላይ በይፋ ማስታወቁን በዋቢነት ያስረዳል።
ከዚያም በሁዋላ በስበስክሪፕሺን የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ለማንሰራራት ብዙ ጥረት ማድረጉን የሚገልጸው ምስክር፣ ብረት ካነሱት ዘንዳ ቀጥተኛ ድጋፍ የማያገኙት ሌሎቹ ምን አማራጭ ሊከተሉ እንደሚችሉ ለጊዜው መረጃ አልሰጠም።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሚዲያ ባለሙያዎችን ሰብሰበው ሲያነጋገሩ ” የቢራና የአልክሆል መጠጥ ማስታወቂያ ይፈቀድልን፣ ገቢ የለንም፣ ከገበያ ልንወጣ ነው ወዘተ” በማለት ጥያቄ ያቀረቡ እንደነበር አይዘነጋም።
በኢትዮጵያ “ተገደለ፣ ፈነዳ፣ ወደመ፣ ፈረሰ፣ አለቁ፣ …” የሚሉ የሚጮሁ መረጃዎች የሚመረጡት አንድም ከሙያ ስነምግባር በማፈንገጥ፣ በሌላም በኩል ተመልካችና አድማጭ ለመሳብ የሚመረጥ አግባብ በመሆኑ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ መናገራቸው አይዘነጋም።
በሌላ በኩል ግን እንደ ትልቅ ድካም የሚጠቀሰው የመንግስት ኮሙኒኬሽን መረጃ ላይ ተኝቶ፣ መረጃ ለሚያፈተልኩ እድሉን በመስጠት ኢትዮጵያዊያን ከውጭ አገር ቀላሉን ጉዳይ “ሰበር ዜና” እየተባሉ እንዲሰሙ በመፈቀዱ ወይም በመመቻቸቱ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት አስተያየት የሚሰጥበት ጉዳይ ነው።
በተመሳሳይ ዜና የአሜሪካ ሬዲዮ መቋረጡ ለኢትዮጵያ የበረከት ያህል መሆኑን የሚናገሩ፣ የአሜሪካ ሬዲዮ ቀደም ሲል የኢትዮጵያን መከላከያ ሰራዊት “የደርግ ሰራዊት” በማለት እንዲበተንና ሜዳ ላይ ወድቆ እንዲለምን ትልቁን ኃላፊነት ወስዶ መስራቱን በቁጭት እያስታወሱ ለፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምስጋና አቅርበው ነበር።
በቅርቡ በተደረገው የህልውና ጦርነት ከትህነግ ጎን ቆማ የነበረችው አሜሪካ በዩኤስ አይዲ በኩል ቀለብ ትሰፍርለት የነበረው ቪኦኤ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ኦሮሚኛና ሶማሊኛ ክፍለጊዜ ላይ ይሰሩ የነበሩ “ኢትዮጵያዊያን” በአገራቸው ላይ የፈጸሙት የክህደት ወንጀል ሊጣራና በልዩ ሁኔታ ተመርመሮ ለትውልድ እንዲቀመጥ የሚጠይቁ እየተደመጡ ነው።
በዚሁ የህልውና ዘመቻ ወቅት አማራ ክልልና አፋር ሲወድም። በርካታ ግፍና የጦርነት ወንጀል ሲፈጸም፣ ሰላማዊ ዜጎች ሲረሸኑ ሚዛን የሳተ ዜና ከማቅርብ በዘለለ ሰላባዎች የሚወንጅሏቸውን ክፍሎች ኢንተርቪው በማድረግ ነጻ የማውጣት ስራ ሲሰሩ እንደነበር ስምና አጀንዳውን እያነሱ የሞገቱ ጥቂት አይደሉም።
“ለአሜሪካ ጥቅም እሰራለሁ” ብለው በመፈረም በቪኦኤ የተለያዩ ቋንቋዎች ከሙያው መርህ በማፈንገጥ የአሜሪካንን ጥቅምና ፍላጎት ለማስፈጸም ሲሰሩ የነበሩ አዲስ አበባ ሲገቡ ካባና ልዩ ምስጋና ሲያቀርቡላቸው የነበሩ አካላት ይህን ለማድረግ ያነሳሳቸው ምክንያት በመርጃና ማስረጃ ሊሞገት እንደሚገባ በቁጭት አስተየየት የሚሰጡ እየበርከቱ ነው። በቪኦኤ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አገራት ድጋፍ የሚሰሩ ጸረ ኢትዮጵያ ሚዲያዎች ላይ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ጥቂት አይደሉም።

