የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝደንት ሆነው መሾማቸው ተሰማ። ዜናው የአቶ ማሞ ምህረቱን መነሳት ተከትሎ የቢሆን ትንተናና የፖለቲካ ዲስኩር ሲያሰሙ የነበሩ ቡድኖችና ግለሰቦችን አስደንግጧል።
ከብሄራዊ ባንክ በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን በግል የኤክስ ገጻቸው ያስታወቁት አቶ ማሞ፣ መንግስትን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይንና አብረዋቸው የሰሩትን ከማመስገንና በቀጣይ ወደ ዓለም ዓቀፍ ተቋም እንደሚያመሩ ፍንጭ ከመስጠት ውጪ ያሉት ነገር አልነበረም።
የአቶ ማሞን መልዕክት በመቀራመት የቢሆን ትንተና ሲሰጡ ያመሹ “ሰውየው ስልታን የለቀቁት ከመንግስት ጋር ያላቸው ግንኙነት ተበልሽቶ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። “አይችሉም፣ የህግ ትምህርት ነው ያላቸው” በማለት አኩራፊዎች የተቹትን ወደኋላ በመመለስ አፈላገው መንግስትና እሳቸው ላይ ውርጅብኝ ያወረዱ ጥቂት አልነበሩም።
ይሁን እንጂ ዛሬ መሾማሸው በይፋ መሰማቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የድሮን ፋብሪካ ሲጎበኙ አብረዋቸው መታየታቸውና የስንብት ኬክ ሲቆርሱ አብረው መሆናቸው ዜናውን ለፖለቲካ ግብአትነት ሲጠቀሙ ለነበሩ ሃያ አራት ሰዓት ባልሞላ ጊዜው ውስጥ የመርዶ ያህል ሆኖባቸዋል።
በሹመት ዜና፣ በምስጋና እንዲሁም ሁሉንም በሚያሳይ የምስል የስንበት ስነስርዓት የታጀበው የአቶ ማሞ ምህረቱ ሽኝት ቀድሞ የተሰማውን ዜና ለፖለቲካ ባዋሉትና የቢሆን ትንተና ሲሰጡ በነበሩ ቡድኖችና ግለሰቦች ይቅርታ አልተጠየቀበትም። ወይም ማስተካከያ ሲያደርጉ አልታየም።
በተመሳሳይ የቀድሞ የኢትዮጵያ የግብርና ሚኒስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ የዓለም ንግድ ድርጅት የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካይ ሆነው መሾማቸው ይፋ ሳይሆን የመነሳታቸው ዜና ሲሰማ በተመሳሳይ የቢሆን ትነተና ሲሰጥ እንደነበር ያስታወሱ፣ መንግስት ኢትዮጵያዊያንን በቁልፍ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት እያስገባ መሆኑ ከምንም በላይ ዜና ሊሆን እንደሚገባ እያመለከቱ ነው።
ኢትዮጵያ በታላላቅ ዓለም ዓቀፋዊ ተቋማቶች ውስጥ ወኪል ስላልነበራት በህልውናው ጦርነት ወቅት ክፉኛ መጎዳቷን የሚያስታውሱ ወገኖች በቅርብ ወራት ውስጥ ብቻ ኢትዮጵያ ሶስት ሰዎችን ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ውስጥ ማስገባት መቻሏ የመንግስት ስትራቴጂ አድርገው እንደሚወስዱት አመልክተዋል።


