ከሌላ ሀገር ጋር ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ትብብር የማድረግ መብት ያለው ማነው?
***********
ይህን ፅሁፍ እንድፅፍ ያነሳሳኝ እዚህ ሰፈር እና በአንዳንድ “ሚዲያዎች” ላይ “ከልሂቅ እስከ ደቂቅ” ይሁነኝ ተብሎ አሊያም በድንቁርና የሚቀነቀን የተሳሳተ እና ጣጠኛ ግንዛቤ ነው። በተለይ አንድ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ዕድሜ ለሚያህል ጊዜ “ፖለቲካ ውስጥ የኖረ” እና “የፖለቲካ ተንታኝ” ተብሎ በየዕለቱ ሚዲያ ላይ ቀርቦ የሚዘባርቅ ሰው አፉን ሞልቶ፦ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ አማፂ ቡድን “ከፈለገው የውጪ ሃይል ጋር ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ትብብር ማድረግ ይችላል” ብሎ ሲበጠረቅ አይቼ ያልገባቸው የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው፤ አውቆ አጥፊዎች ደግሞ የጥፋታቸው ተመጣጣኝ ዋጋ ምን ያህል እንደሚሆን እንዲያውቁት ነው።
በዘመናዊው የሀገረ-መንግስት ስርዓተ-ዓለም (a.k.a. the Westphalian State System) ውስጥ እንዲሁም ከህግ እና ከመርህ አንፃር ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ትብብር ለሉአላዊ ሀገራት የተተው መብት (prerogative) ነው። ሀገራት ብሄራዊ ጥቅማቸውን እና ደህንነታቸውን ለማጠናከር እና ለማሳለጥ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ትብብሮችን በይፋ ወይም ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ሊመሰርቱ ይችላሉ። ይህን ሲያደርጉ ለማንም ማብራሪያም ሆነ ማስተባበያ የመስጠት ግዴታ የለባቸውም። ይሁንና በሀገራት መሀከል ሊፈጠር የሚችልን security dilemma ለመቀነስ የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን በመጠቀም የትብብራቸውን አላማ (intention) ሊገልፁ ይችላሉ።
በተቃራኒው በአንድ ሉአላዊ ሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀስ ፖለቲካዊም ሆነ ሲቪክ ተቋም፤ ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ትብብር ማድረግ አይችልም። ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው አስፈላጊ የሲቪክ ትብብሮች ማድረግ ግድ ሲሆንም በሀገሪቱ መንግስት ዕውቅና እና ፈቃድ ላይ ብቻ ተመስርቶ ነው ሊደረግ የሚችለው። በተመሳሳይ አንድ ሀገር በሌላ ሀገር ከሚገኙ ፖለቲካዊ እና ሲቪክ ተቋማት ጋር ያለ ሀገራቸው መንግስት ዕውቅና እና ፈቃድ ግንኙነትም ሆነ ትብብር ማድረግ አይችልም። ይሄ በተፃፈውም ባልተፃፈውም ህግ የታወቀ መርህ ነው። ይህን መተላለፍ በአንድ ሀገር የውስጥ ጉዳይ ገብቶ እንደ መፈትፈት የሚቆጠር እና ጣጣ የሚያስከትል ነገር ነው። ይሁንና ሀገራት ግንኙኘታቸው በሚበላሽበት ጊዜ ከሚጎነታተሉባቸው መንገዶች አንዱ ይህን መርህ በሙሉ ወይም በከፊል መጣስ ነው።
በምሳሌ ላስረዳ፦ በሰሜኑ ጦርነት ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ጋር ታክቲካል ወታደራዊ ትብብር አድርጎ ነበር። ያም የሆነበት ምክንያት ህወሐት በሁለቱም ሀገራት ላይ clear and present የብሄራዊ ደህንነት ስጋት በመደቀኑ ነበር። ትብብሩ የተደረገው በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ድንበር ተሻጋሪ (transnational) ወታደራዊ እንቅስቃሴ ስለነበረ ጭምር ነው።
ይህ ትብብር ታክቲካል ግቡን ካሳካ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ፈርሷል። አንዳንዶች በወቅቱ ወይም አሁን “መንግስት ከኤርትራ ጋር ወታደራዊ ትብብር ማድረግ ከቻለ እኛም እንችላለን። መብታችን ነው” ሲሉ ይደመጣሉ። ለዚህ አይነቱ የአላዋቂ መከራከሪያ መልሱ አጭር እና ቀጥተኛ ነው፦ ከኤርትራም ሆነ ከሌላ የውጪ ሀይል ጋር ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ትብብር ማድረግ አትችልም! መብትህም አይደለም! ይሄን ተላልፈህ ብትገኝ the state has every right to take any measure that it deems necessary and proportional! ስለዚህ በሰማይ እና በምድር ከሚያዘንብብህ የእሳት በረዶ በተጨማሪ፤ በአካል ይዞ፣ በሀገር ክህደት ወንጀል ከስሶ፣ በሞት ወይም በዕድሜ ልክ እስራት ሊቀጣህ ይችላል! በዚህ ላይ መንግስት ላይ ጦር መምዘዝህ የሚያስከትለውን ተጠያቂነት ስትጨምርበት የሚጠብቅህን ጣጣ መገመት አይከብድም።
ይህ እንግዲህ ሀገሩ ጦቢያም ሆነ ራሺያ ቻይናም ሆነ ካናዳ፤ በስልጣን ላይ ያለው ሀይል ደግሞ አፄያዊም ሆነ ደርግ፤ ብልፅግናም ሆነ ኢህአዴግ ተፈፃሚነቱ የፀና መርህ ነው።
እና ምን ለማለት ነው…በደንቆሮ ምክር፣ በደም-ፍላት ወይም በእብሪት ተነሳስተህ ከሌላ ሀገር ወይም የውጪ ሀይል ጋር “ፅምዶ” በለው ጥምረት ወይም tactical alliance ውስጥ ከገባህ፤ ለመንግስት ያለውን ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ እና ሌሎች በራሱ መንገድ አዋጭ ናቸው ያላቸውን አማራጮች በሙሉ ሳይሰስት እንዲጠቀም በቂ justification እየሰጠኸው ነው።
ለእኔ ለተራው ዜጋ ደግሞ አሰላለፌን ከማን ጋር ማድረግ እንዳለብኝ ግልፅ መልዕክት እያስተላለፍክልኝ ነው! ገና ለገና የመንግስት ፖሊሲ እና አመራር አልተመቸኝም ወይም አልጣመኝም ብዬ የሃገሬን ብሄራዊ ጥቅም፣ ደህንነት እና ክብር ለአደጋ ከሚያጋልጥ ባንዳ ጋር አልበነድድም! ባይሆን አፍንጫህን ለመስበር በተጨበጠው መዳፍ ላይ ጓንት እንደማጥለቅ ያለ አነስተኛ አስተዋፅኦም ቢሆን አደርጋለሁ እንጂ! Let that sink in።

