አሜሪካ በኢትዮጵያ በ10 ቢሊዮን ዶላር ለሚገነባው የአፍሪካ ትልቁ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገባች። ይህም የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአፍሪካ ቀንድ የመጀመሪያው ትልቅ የቢዝነስ ተነሳሽነት ተደርጎ ተወስዷል።
የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ሀገሪቱ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኝነቷን አስታውቀዋል። እንደ ቢዝነስ ኢንሳይደር አፍሪካ ዘገባ፣ ቡሎስ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን በፕሮጀክቱ እንደሚሳተፍ እና ከቦይንግ ጋር በመተባበር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በአፍሪካ ባሉ ሌሎች ሥራዎች ላይ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገንባው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት በሁለት መዕራፍ የሚከናወን ሲሆን የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል። ሁለተኛው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ አቅሙን ወደ 110 ሚሊዮን መንገደኞች ወደ ማስተናገድ ከፍ የሚል ሲሆን በዓመት 3.73 ሚሊዮን ቶን ጭነት የሚያጓጉዝ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በ34 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ የሚያርፈው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታው ሲጠናቀቅ፣ በመጠንም ሆነ በማስተናገድ አቅም የጆሃንስበርጉን የኦ.አር. ታምቦ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን በመብለጥ በአፍሪካ ትልቁ የአውሮፕላን ማረፊያ ይሆናል ተብሏል።
ከግባታው መጠናቀቅ በኋላ የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሀገር ውስጥ በረራዎችን ብቻ የሚያስተናግድ ሲሆን፣ መጨናነቅንም ያቀላል ተብሎ ይጠበቃል። የአውሮፕላን ማረፊያው ሆቴሎች፣ የገበያ ማዕከላትና የመዝናኛ ስፍራዎችን የሚያካትት ሲሆን፣ የአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እድገትን የበለጠ የሚያሳድግ ከመሆኑም ባሻገር ኢትዮጵያን የአቪዬሽን ማዕከልነትን ያጠናክራል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በ2018 ዓ.ም ኅዳር ወር መጨረሻ ለመጀመር እቅድ መያዙን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው መግለጻቸው ይታወሳል። ግንባታው በአምስት ዓመታት ውስጥ ተጠናቆ በ2023 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የበረራ አገልግሎት እንዲጀምርም ገልጸዋል። አየር መንገዱ ለፕሮጀክቱ ከሚያስፈልገው 10 ቢሊዮን ዶላር 20 በመቶ የሚሆነውን እንደሚያቀርብ እና ቀሪው ደግሞ ከሌሎች አበዳሪዎች እንደሚገኝ አስታውቋል።
የአፍሪካ ልማት ባንክ ባሳለፍነው ነሐሴ ወር ለአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ 500 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል። ባንኩ ግንባታው ለአውሮፕላን ማረፊያው ከሚያስፈለገው 10 ቢሊየን ዶላር፣ 8 ቢሊዮን ዶላር ለማፈላለግ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ስምምነት መፈራረሙም ይታወሳል።



