የራስደስታ ዳምጠው ሆስፒታል የመልካም አስተዳደርና የብልሹ አሰራር እንዳለበት በርካታ ጥቆማዎችና ምልክቶች አሉ። ሰሞኑን ይመረቃል የተባለው አዲሱ ባለ አምስት ፎቅ ሕንጻ ጉዳይ ብዙ እያነጋገረ ባለበት ወቅት ነው አስተዳደሩ ለገምጋሚዎች ያዘጋጀውን ድግስ ራሱ እንደበላው የተተቆመው።
የኢትዮሪቪው የአዲስ አበባ ዘጋቢ በቅጥር ግቢው ውስጥ ተገኝቶ እንደታዘበው ክትፎ፣ ቅቅል፣ ጥብስ፣ ሁለት ሙክት ፍየሎች ታርደው በልዩ ሁኔታ ተዘጋጅቶ የቀረበው ትናንት መስከረም 27 ቀን 2018 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ለተላኩ ገምጋሚዎች ማበበያ ነበር።
ከነበርካታ ጉዱ ተሸፋፍኖ ለምረቃው ከንቲባ አዳነች አቤቤን እየተጠበቅ ባለው አዲሱ ሕንጻ ውስጥ የተዘጋጀው ድል ያለ ድግስ ያልተጠበቀ ምላሽ ያገኘው ከገምጋሚዎቹ ነበር።
ዘጋቢያችን እንደታዘበውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እንዳስታወቁት፣ ገምጋሚዎቹ ድግሱን እንዲታደሙ ሲጋበዙ ” ልንበላ አልመጣንም። የመጣነው ለስራ ነው” በማለታቸው ድግሱን ያዘጋጀው የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ፣ ሜዲካል ዳይሪክተርና የተጋበዙ ሜትሮኖች፣ እንዲሁም የአስተዳደር አካላት ራሳቸው በልተውታል።
ከገምጋሚዎቹ መካከል አንደኛዋ በሆስፒታሉ ውስጥ ያለውን አሰራርና ብልሹ ተግባራት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ይህ ሊፈጠር እንደቻለ ለመረዳት ተችሏል።
የራስደስታ ሆስፒታል አዲስ ያሰገነባው ሊመረቅ ቀን ተቆርጦ ከንቲባዋ እንደሚመጡ ከተነገረ በሁዋላ ህንጻው ውሃ ሞልቶት፣ ከስር የፍሳሽ ማስወገጃ ባለመኖሩ ግቢው ዳግም መቆፈሩን፣ ከህንትሳው የወጣው ውሃ መጋዘን ማበላሸቱንና ንብረት ማውደሙን በምስል አስደግፈው ተቆርቋሪዎች ለዝግጅት ክፍላችን ልከዋል።
የዝግጅት ክፍላችን ይህንኑ መረጃ በማሰባሰብ ሪፖርት ለማቅረብ እየሰራ ሲሆን፣ አዳነች አቤቤ ለምረቃ ሲመጡ ሰራተኖችን እንዲያነጋገሩ፣ ሕንጻው ላይ ያለው ግድፈት ተለባብሶ እንዳይታለፍ፣ ከምንም በላይ በግቢው ውስጥ ያለው ብልሹ አሰራር መፍትሄ እንዲበጅለት ገምጋሚው ቡድን በፍጥነት መረጃውን እንዲልክላቸው ሰራተኞች ጠይቀዋል።
በራስደስታ ሆስፒታል ያለ አግባብ የተባረሩ፣ ለምን አስተያየት ሰጣችሁ በሚል የተቀጡ፣ በክፍያ የሚፈጸሙ ጉዳዮችን ጨምረው ዝርዝር ለላኩልን አካልት ምስጋና እያቀረብን የክልሉን ጠና ቢሮ በማነጋገር ሙሉውን ሪፖርት እንደምናትም ከወዲሁ እናሳውቃለን። ተጨማሪ መረጃ ያላችሁ በቴሌግራም ገጻችን ብትልኩልን እንደሚደርሰን ለማሳሳብ እንወዳለን።

