በVOE News | ሐምሌ 2 ቀን 2018 ዓ.ም. አሜሪካ በኢራን ላይ አዲስ እና ሰፊ የወታደራዊ ጥቃት መጀመሯን አስታወቀች። ዋሽንግተን እርምጃውን የወሰደችው ኢራን ጦርነቱን ለማቆም የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ (Memorandum of Understanding) በመጣሷ እና በዓለም የንግድ መርከቦች ዋና መተላለፊያ ከሆነው የሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ በንግድ መርከቦች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ተከትሎ መሆኑን ገልጻለች።
የአሜሪካ ማዕከላዊ እዝ (CENTCOM) እንደገለጸው፣ ከ80 በላይ የኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች በጥቃቱ ተመተዋል። ከተመቱት መካከል የአየር መከላከያ ሥርዓቶች፣ የሚሳይል ማስወንጨፊያዎች፣ የድሮን ማዕከላት፣ የባሕር ኃይል ተቋማት እና የትዕዛዝ ማዕከላት ይገኙበታል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቱርክ በተካሄደው የኔቶ ጉባኤ ላይ ሲናገሩ፣ ኢራን ስምምነቱን በመጣሷ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንደፈረሰ ገልጸው፣ ተጨማሪ ጥቃቶች ሊከተሉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል። የዓለም አቀፍ የባሕር መጓጓዣ ነፃነትን ለማስጠበቅ አሜሪካ እርምጃዋን እንደምትቀጥልም አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ኢራን የአሜሪካን ጥቃት “ግልጽ የጦርነት ድርጊት” ሲትል በማውገዝ ከባድ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቃለች። አሜሪካ ራሷ ስምምነቱን እንደጣሰች በመክሰስ፣ በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ማዕከላት ላይ የበቀል ጥቃቶች መፈጸማቸውንም አስታውቀዋል።
የሁለቱ ሀገራት ውጥረት መባባሱ በዓለም የኃይል ገበያ ላይ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል። በሆርሙዝ ባሕረ ሰላጤ የመርከብ እንቅስቃሴ ደህንነት ላይ ያለው ስጋት እየጨመረ ሲሆን፣ የዓለም የዘይት ዋጋም ከፍ ማለቱ ተዘግቧል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደገና ለማስጀመር የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ቢቀጥሉም፣ ዋሽንግተንና ቴህራን እርስ በርሳቸው የስምምነቱ መፍረስ ኃላፊነት እየተወራረሱ በመሆኑ ቀጣዩ ሁኔታ አሁንም አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል።
ምንጮች: Reuters, Associated Press, U.S. Central Command (CENTCOM)
በVOE News – “Ethiopia is the Center”

