የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገርና ለህዝቡ ጥቅም ሲባል በሀገራችን ሰላምን ለማስፈንና ለማጽናት በትጋት እንሰራለን አሉ። ፓርቲዎቹ ‘ሰላምን ማስፈንና ማጽናት’ በሚል መሪ ሀሳብ በቢሾፍቱ ከተማ ባካሔዱት ምክክር ላይ ለሀገር ሰላም በጋራ እንደሚሰሩ የቢሾፍቱ ቃል ኪዳን በሚል ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
የቢሾፍቱ ቃል ኪዳን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሠላምን በማስፈንና በማጽናት የሚኖረን ሚና ላይ የቢሾፍቱ ቃል ኪዳን (ዲክላሬሽን)
ሰላምን በማስፈንና በማጽናት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ላይ የሚመክር የሠላም ኮንፍረንስ መድረክ አካሂደናል። ለመድረኩ በጋራ ም/ቤት ዕቅድ መሠረት የተለያዩ ዝግጅቶች ሲደረጉ የቆየ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ከኢፌዴሪ ሠላም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ዕውን ማድረግ ተችሏል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሠላምን ማስፈንና ማጽናት በሚል መሪ ሃሳብ የሚመክር ሀገራዊ መድረክ በመዘጋጀቱ ምስጋናችን የላቀ ነው።
በመድረኩ ሀገራዊ የሠላም አውድና እና ዓለም አቀፍ ገጽታውን በንድፈ ሃሳብና በተለያዩ ተሞክሮዎች ለሀገራችን ሠላም መስፈንና ማጽናት ባለው ፋይዳ ላይ በምሁራን በቀረቡ የውይይት ሰነዶች ላይ ተመስርተን የሠላምን ምንነትና መገለጫዎችን፣ በሰላም ላይ ቀጠናዊ እና ዓለማዊ ሁኔታ የሚኖረውን ተጽዕኖ እንዴት መቋቋም ይቻላል? የሰላም ተዋኒያን ማንነት እና ሃላፊነት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና እና በመጨረሻም የሀገራችን የሰላም ችግር መነሻዎችና የመፍትሄ አቅጣጫ ላይ በጥልቀት ተወይተናል።
ይህም እንዲሳካ በውይይት ቡድን በመከፋፈል በዝርዝር ከተመለከትን በኋላ በውይይት ነጥቦች ዙሪያ ተቀራራቢ ግንዛቤ ለመያዝ እድል አግኝተናል። በዚህም፡-
- ሠላም የሁሉ ነገር መሠረት መሆኑን፣
- እኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሠላማዊ የፖለቲካ ትግል ተምሳሌት መሆናችንን በመገንዘብ፣
- ለቆምንለት የህብረተሰብ ክፍል፣ ሃገር እና ትውልድ ሰላም እንዲጸና እንደ ፖለቲካዊ መሪዎች ሃላፊነት መወጣት እንዳለብን በማመን፣
- ሠላም ለዲሞክራሲ ስርኣት ግንባታ ያለውን የማይተካ ሚና በመገንዘብ፣
- ይህን እምነታችንን በዚህ የቢሾፍቱ የቃል ኪዳን መግለጫ ይፋ ስናደርግ ለተግባራዊነቱ የባለድርሻ አካላትም ሚናቸውን እንዲወጡ በእነዚህ ባለ 7 አንቀጽ የቃል ኪዳን ነጥቦች ጥሪያችንን እናቀርባለን።
አንቀጽ 1: ሠላማዊና የሠለጠነ የፖለቲካ አካሄድ የመከተል ቃል ኪዳን
1.1. የፖለቲካ ዓላማችንን በዲሞክራሲያዊ እና በሕግና በስርዓት እናከናወናለን።
1.2. ጸጥታን በማደፍረስ፣የስም ማጥፋትና ጥላቻ እንዲሁም ለሰው ህይዎትና ንብረት መጥፋት ምክንያት ባለመሆን ለሰላም እንተጋለን።
አንቀጽ 2:
ለዲሞክራሲ ተቋማትና እሴቶች ክብር የመስጠት ቃል ኪዳን
2.1. ሕግና ሥርዓት፣ የህዝብ ውሳኔ ወሳኝነት፣ የምርጫ ሂደቶችና ውጤት እንዲከበሩ።
2.2 በውሳኔዎች ላይ ልዩነት ቢኖር እንኳ ህጋዊነትን በማክበር አቋማችንን ማራመድ።
አንቀጽ 3: ለአካታችነት፣ ለሀገራዊ መግባባትና ብሄራዊ ጥቅም አብሮ የመቆም ኪዳን
3.1. ያሉንን ልዩነቶችን ክብርና ልዩ ትኩረት በመስጠት ለህብረብሄራዊነት እሳቤ ግንባታ ለመስራት ተስማምተናል።
3.2. የወጣቶች፣ የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እንዲያድግ በትኩረት እንሰራለን።
3.3. ለብሄራዊ ጥቅም አብሮ የመቆም የፖለቲካ ባህል እንገነባለን።
አንቀጽ 4:
ለዴሞክራሲያዊ መልካም አስተዳደር መስፈን የመስራት ቃል ኪዳን
4.1. በአጀንዳ፣ በፖሊሲ፣ በችሎታ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ለመገንባት እንሰራለን።
4.2. የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰብና ፍላጎት መኖር እንደ ጤናማ ዴሞክራሲ ምልክት እንቀበላለን።
አንቀጽ 5:
የግጭት አያያዝ እና የሰላም ግንባታ ውጤታማነት የመስራት ቃል ኪዳን
5.1. በየፓርቲዎቻችን ውስጥና በሌሎች ፓርቲዎች መካከል ለግጭቶች ምክንያት የሚሆኑ ጉዳዮች ላይ የመፍትሄ ሥርዓቶችን እንገነባለን።
5.2. በማህበረሰብ፣በአካዳሚያ፣በተለያዩ መድረኮች እና ከፖለቲካ አመራሮች ጋር በሚካሄዱ የሰላም ውይይቶች በአጋርነት እንሳተፋለን።
አንቀጽ 6:
የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ የማዳበር ቃል ኪዳን
6.1. በመንግስት እንዲሁም በፓርቲያችን ውስጥ ግልጽነት፣ የሐሳብ ነጻነትና መተማመን እንዲጎለብት እንተጋለን።
6.2. የህዝብ ተሳትፎ የሚገድብ ሥራ እና ተቋማዊነት የሚጎዳ የፖለቲካ አካሄድ በጋራ እንታገላለን።
አንቀጽ 7:
ለብሄራዊ ጥቅም እና ለዴሞክራሲ ስርዓት የመጽናት ቃል ኪዳን
7.1. በሰላም፣በውጫዊ ችግሮች፣ በብሄራዊ ምርጫ እና በመንግሥት ልማት አካል እንደ አንድ አካል እንሰራለን።
7.2. በኢትዮጵያ የዜጎችና ህዝቦች ክብር እና በሀገራች የጋራ ዕጣ ፋንታችን ላይ በጋራ በመቆም ለተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት ለማጽናት እንሰራለን።
መደምደሚያ መግለጫ
ይህ የቢሾፍቱ የቃል ኪዳን መግለጫ፣ እኛ እንደፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከፍተኛ የሰላም መሪነትን፣ ማህበራዊ ሀላፊነትን እና ከሀገራዊ የጋራ ፍላጎትና ጥቅም በመነሳት ለመስራት ካለን የፖለቲካ ቁርጠኝነት ላይ የተመሰረተ ነው።
ከዛሬ ጀምሮ ፖለቲካዊ ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ለአገርና ለህዝቡ ጥቅም ሲባል በሀገራችን ሠላምን ለማስፈንና ለማጽናት በትጋት ለመስራት እንተጋለን።
ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አውድ ውጪ ያላችሁ የፖለቲካ ሃይሎችና የታጠቁ ቡድኖች ልዩነቶችን በሠላማዊ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈታ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ለስኬታማነቱም ሚናችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን።
በሀገራችን ሠላምን ለማስፈንና ለማጽናት የሚያግዙ ስልቶችን ተግባራዊ በማድረግ ከሚመለከታቸውና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበትና በትብብር ለመስራት ተስማምተናል።
ሰላም የሁሉ መሰረት ነው!!! ሐምሌ 17/2017 ዓ.ም ቢሾፍቱ

