ከሰሞኑ ቅዱስ ፓትርያርኩ ” እንደራሴ እንዲሾምላቸው በደብዳቤ ጥያቄ አቀረቡ ” በሚል በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲዘዋወር ነበር። ይህንኑ ተከትሎ ጽሕፈት ቤታቸው ወሬው ተራ መሆኑን አስታውቋል።
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ተግባራትን ለመምራት ሆነ ለማከናወን የማያስችል ምንም ዓይነት የጤና እክል እንዳልገጠማቸው አሳውቋል።
ልዩ ጽሕፈት ቤቱ ፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ላለፉት ተከታታይ ዓመታት ወደ ሰሜን አሜሪካ በማምራት የሕክምና ክትትል ሲያደርጉ እንደቆዩ ፤ በቅርቡም ተመሳሳይ ጉዞ አድርገው ጳጉሜን 1 ቀን 2017 ዓመተ ምሕረት ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ መመለሳቸውን አስታውሷል።
የመስቀል ደመራ በዓልንም በመስቀል አደባባይ ተገኝተው በማክበር ለመላው ሕዝበ ክርስቲያን አባታዊ ትምህርተ ወንጌል ፣ ቃለ ምእዳንና ቡራኬ እንዳስተላለፉም አስታውሷል።
እንዲሁም ቤተክርስቲያኗ በየዕለቱ የምታከናውናቸው መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊ እና ዓለም አቀፍ ተግባራትን በጽሕፈት ቤታቸው ሆነው በአባትነት እየመሩ በተሟላ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።
” ይሁን እንጂ ድብቅ አጀንዳ ይዘው ሐሰተኛ መረጃን በማሰራጨት መደበኛውን የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ ማደናቀፍ ዓላማቸው ያደረጉ አካላት በማኅበራዊ የትስስር ገጾቻቸው ባጋሩት ፍጹም ከእውነት የራቀ መረጃ ውሉደ ክህነት እና በጎ ሕሊና ያላቸው ምእመናን በእጅጉ መጨነቃቸውን ለመገንዘብ ችለናል ” ብሏል።
” ስለሆነም ቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ተግባራትን ለመምራትም ሆነ ለማከናወን የማያስችል ምንም ዓይነት የጤና እክል ያልገጠማቸው፤ ከዚሁ ጋር በተያያዘም ያቀረቡት ጥያቄ የሌለ መሆኑን እንገልጻለን ” ሲል ልዩ ጽሕፈት ቤቱ አሳውቋል።

