በቀድሞ አጠራር ወሎ ጠቅላይ ግዛት ፣ ደሴ ዙሪያ፣ ከድጆ ውስጥ ምጣን ጎራ በተባለች መንደር የካቲት 21 ቀን 1930 ዓ/ም ተወለዱ ። ሜጄር ጄኔራል ሁሴን አህመድ ገና በልጅነታቸው አባታቸው አቶ አህመድ አሊ ከድጆን ለቅቀው ደሴ ከተማ በመግባታቸው ህጻኑ ሁሴን የከተማ ልጅ ለመኾን በቁ ። ደሴ እንደገቡ የፊደል ትምህርታቸውን ጨርሰው ማንበብ እንዳጠናቀቁ አባታቸው የአስኳላ ትምህርት እንዲማሩ አደረጓቸው።
#የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በንጉሥ ሚካኤል ትምህርት ቤት እና በወይዘሮ ስሒን ትምህርት ቤት ተምረው የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በማለፋቸው በ1946 ዓ/ም አዲስአበባ ከሚገኘው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገቡ። በውቅቱ ተፈሪ መኮነን ከየክፍለ ሐገሩ ጎበዝ ተማሪዎችን ሰብስበው ያስተምሩ ነበር። ተማሪው ሁሴን “የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ማጠናቀቂያ ዓመት ላይ ( በ1949 ዓ/ም) ተማሪዎች አመጽ በማስነሳታቸው በአመጹ ተጠርጥሬ ወደ ሐረር መድኀኒኔዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተዛውሬ እንድጨርስ ኾንሁ ” ይላሉ።
#ተማሪው ሁሴን የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በማለፍ በወርኀ መስከረም 1950 ዓ/ም “ኢትዮ ስዊድን ሕንጻ ኮሌጅ” በመባል ከሚታወቀው ኮሌጅ በመግባት ትምህርታቸውን መከታተል ጀመሩ። በዚያው ዓመት የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት መገባደጃ ላይ በሐገሪቱ ላይ አዲስ ነገር ተከፈተ፣ የኢትዮጵያ ጦር አካዳሚ። የኢትዮጵያ ጦ። አካዳሚ ከሁሉም ትምህርት ቤቶች ብቁ ተማሪዎችን መልምሎ ማሰልጠን ይፈልግ ነበር። ተማሪው ሁሴን ከመጀመሪያዎቹ 40 የኢትዮጵያ ጦር አካዳሚ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አንዱ በመኾን የኢትዮጵያ ጦር አካዳሚን ተቀላቀሉ።
#ለውትድርና የሚያበቃውን ስልጠና በሚገባ አጠናቅቀው መስከረም 21 ቀን 1953 ዓ/ም አፄ ኃይለሥላሴ በተገኙበት የምክትል መቶ እልቅና እና የሁለተኛ ዓመት የኮሌጅ ዲፕሎም በማግኘት ” ከራስ በፊት ለሐገርና ለንጉሠ ነገስት” በሚል የመሐላ ቃል ተመረቁ። ጥቅምት ወር 1953 ዓ/ም በሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በአሰልጣኝነት የተመደቡት ሁሴን አህመድ ከሦስት ዓመታት ሥራ በኋላ ጀምረውት የነበረውን የሁለት ዓመት ኮሌጅ ትምህርት ለመቀጠል አዲስ አበባ ኮሌጅ በመግባት በሕዝብ አስተዳደር ዘርፍ በቢኤ ዲግሪ ተመረቁ።

#በወርኀ መስከረም 1958 ዓ/ም በሐገር መከላከያ ሚኒስቴር ትዕዛዝ ለተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ የሰላም ተቆጣጣሪ ልዑክ አባል በመኾን ሕንድ፣ ባኪስታን በመኼድ ለስድስት ወራት የቆዬ የሰላም ጥበቃ ግዳጃቸውን ተወጥተዋል። ወደ ሐገራቸው እንደተመለሱ የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት የአሰልጣኝነት ሥራቸውን ቀጠሉ። በዓመቱ ጳጉሜ 1959 ዓ/ም የሻምበልነት ማዕረግ ደረቡ። በ 1960 ዓ/ም የምድር ጦር ጠቅላይ መምሪያ መኮነኖች አስተዳደር ቢሮ በመመደባቸው ወደ አዲስ አበባ ገቡ።
#በወርኀ ታኀሳስ 1967 ዓ/ም ለከፍተኛ መኮነንነት የአስተዳደር ትምህርት ለመማር ወደ አሜሪካ በማቅናት የሌተናል ኮሎኔልነት ማዕረግ ተቀበሉ።ሚያዚያ 1969 ዓ/ም የሶማሊያ ወረራ ወቅት የሊሚሺያ ( ሚሊሻ) ብርጌድ አዛዥ በመኾን እናት አገርን ታድገዋል። የሶማሊያ ጦርነት ገና ሳይጠናቀቅ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ሕወሓት እና ሻቢያ የመገንጠል ጥያቄ ይዘው ተነሱ። እኒኽ የጦር መኮነን በሐምሌ ወር 1969 ዓ/ም ለወታደራዊ ግዳጅ ብርጌድ ጦር ይዘው በአውሮፕላን ኤርትራ ገቡ። ከሐምሌ 1969 ዓ/ም እስከ 1983 ዓ/ም ድረስ የሐገርን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ የኤርትራ የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት የጦር አዛዥ በመኾን እናት አገራቸውን ጠብቀዋል። የሜጄር ጄኔራነት ማዕረግ ያገኙትም ኤርትራ በረሃ ውስጥ ነው።
#የጦር መኮነኑ በኤርትራ ውስጥ በነበሩበት ዘመን በብዙ የኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ ሲኾን ለአብነትም፣
1. የግንቦት 8 1981ዓ/ም ተሞክሮ በከሸፈው መፈንቅለ መንግስት የሁለተኛ አቢዮታዊ ሰራዊት ዋና አዛዥ የነበሩት የሜጀር ጀነራል ደምሴ ቡልቶ መገደል ተከትሎ ኤርትራ የነበረውን ግዙፋና ጠንካራውን ሁአሰን በዋና አዛዥነት እስከ ግንቦት 1983 ዓ/ም መርተዋል።
2. በ1973 ዓ/ም በጥቅምት ወር የውቃው ዕዝ የ506ኛው ግብረ ኃይል ምክትል አዛዥ በመኾን በሱዳን ጠረፍ በአልጌና እና ቃሮራ በኩል የነበረውን ግዳጅ በአግባቡ ተወጥተዋል።
3. በ1973 ዓ/ም በጥቅምት ወር የውቃው ዕዝ የ506ኛው ግብረ ኃይል ምክትል አዛዥ በመኾን በሱዳን ጠረፍ በአልጌና እና ቃሮራ የነበረውን ግዳጅ በአግባቡ ተወጥተዋል።
#በመጨረሻም ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ/ም ማክሰኞ ዕለት መንግሥቱ ኃይለማርያም መኮብለላቸውን ሌ/ጄኔራል አዲስ ተድላ ለሜጄር ጄኔራል ሁሴን አህመድ ይነግራቸዋል። ደጀን የሚኾን ጦር ከአሰብ ለማጓጓዝ እጅግ አስቸጋሪ በመኾኑ የኤርትራ ጉዳይ ማክተሙን ይገነዘባሉ። ሻቢያ አስመራን ለመያዝ ተቃርቧል፣ ሕወሓት በቡሬ ወለጋ ብሎ አምቦ ገብቷል። የጦር መኮነኑ ራሳቸውን ማትረፍ እንዳለባቸው ወሰኑ። በሱዳን በኩል ለመውጣት አስበው የሱዳን መንግስት እጃቸውን ይዞ ለሻቢያ እንደሚሰጣቸው የተገነዘቡት የጦር መኮነን ግንቦት 15 ቀን 1983 ዓ/ም ጉዟቸውን ወደ የመን አድርገው የሳውዲ አረቢያ ለአራት ዓመታት ከቆዩ በኋላ ኑሯቸውን በሐገረ አሜሪካ አድርገዋል።
#ጀግናው የጦር መኮነን ወይዘሮ በለጡ ምህረቱን ጥቅምት 17 ቀን 1960 ዓ/ም አግብተው ሦስት ልጆችን ወልደዋል። ሜጄር ጄኔራል ሁሴን አህመድ በ1997 ዓ/ም “መስዋዕትነት እና ፅናት” በተከታይም “ማር እና እሬት” የተሰኙ መጽሐፍ ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል።
ክብርና ሞገስ ለጀግኖቻችን!! ንበጌታ በለጠ አብዮታዊው_ሰራዊት_ገፅ

