የእስራኤል እና የኢራን ጦርነት ተባብሶ በቀጠለበት በዚህ ወቅት፤ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ጋር በሞስኮ ተገናኝተው መክረዋል። አሜሪካ በኢራን ላይ የወሰደችው ጥቃት ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ አይደለም ሲሉ የኔቶ ዋና ጸሃፊ ማርክ ሩት አስታውቀዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት አሜሪካ በኢራን ላይ ያደረሰችውን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን፤ ሩሲያ ለኢራን ሕዝብ ድጋፍ እንደምታደርግ ለልዑካን ቡድኑ አረጋግጠዋል።
ፑቲን ከኢራን ልዑካን ቡድን ጋር ሲገናኙ የሚያሳይ አጭር ቪዲዮ በክሬምሊን የተለቀቀ ሲሆን፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሰርጌ ላቭሮቭ እና ዩሪ ኡሻኮቭ፣ ከፍተኛ ረዳት እና በዋሽንግተን የቀድሞ የሩሲያ አምባሳደር በውይይቱ ላይ ተገኝተዋል።
በውይይቱ ላይ “ይህ በኢራን ላይ የሚፈጸመው የጥቃት እርምጃ ምንም አይነትሕጋዊ መሰረት እና ምክንያት የለውም።” ያሉት ፑቲን፤ “ከኢራን ጋር ለረጅም ጊዜ የቆየ ወዳጅነት እና አስተማማኝ ግንኙነት አለን፡፡ እኛም በበኩላችን የኢራንን ሕዝብ ለመደገፍ ጥረት እያደረግን ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፑቲን ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት መሀመድ አል ናህያን እና የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ጋር የስልክ መወያየታቸውንም ለኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።
አራግቺ በበኩላቸው ፑቲን ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው፤ ሩሲያ “በታሪክ ትክክለኛ ጎን ላይ ነች” ብለዋል።
በተጨማሪም በቴህራን እና በሞስኮ መካከል ያለው የጠበቀ ግንኙነት፤ “በቅርብ ዓመታት ውስጥ ይበልጥ እየተጠናከረ መጥቷል” ሲሉ መግለጻቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ኢራን እ.ኤ.አ በ2022 ሩሲያ ሙሉ ወረራ በዩክሬን ላይ ከከፈተች በኋላ፤ ከሩሲያ ጠንካራ ደጋፊዎች መካከል አንዷ ሆናለች።
በዚህ ኢራን ለአጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤሎች እና በሺዎች የሚቆጠሩ “ሻሄድ ድሮኖችን” ጨምሮ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ለሩሲያ የሰጠች ሲሆን፤ በሩሲያ ውስጥ የድሮን ፋብሪካ መገንባቷንም የአሜሪካ ባለስልጣናት ገልጸዋል።
ሞስኮ በበኩሏ ከእስራኤል ጋር በነበረችበት ግጭት እና ከአሜሪካ ጥቃት በኋላ ከኢራን ጎን ቆማለች።
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ “ከኒውክሌር መርሃ ግብር ጋር በተያያዘ ሩሲያ አጋራችን ነበረች፡፡ እኛን ረድታናለች” ያሉ ሲሆን፤ በተጨማሪም ሩሲያ በኑውክሌር ንግግሮች ላይ ተገኝታለች እና ትልቅ ሚና መጫወቷን በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
ሩሲያ በደቡባዊ ኢራን የሚገኘውንና የአገሪቱ ብቸኛ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የሆነውን የቡሼህር የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ገንብታ እየሰራች መሆኑም ተነግሯል፡፡
ፑቲን ባለፈው ሳምንት ወደ 200 የሚጠጉ የሩሲያ ባለሙያዎች በተቋሙ ውስጥ እንደሚገኙየገለጹ ሲሆን፤ እስራኤል ደህንነታቸውን “ለማረጋገጥ” በመስማማቷ አመስግነዋል።
አሜሪካ በኢራን ላይ የወሰደችው ጥቃት ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ አይደለም
አሜሪካ በኢራን ላይ የወሰደችው ጥቃት ዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ አይደለም ሲሉ የኔቶ ዋና ጸሃፊ ማርክ ሩት አስታውቀዋል።
የኔቶ የኔቶ ዋና ጸሃፊ ማርክ ሩት በመግለጫቸው ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን በኒውክሌር ጣቢያዎች ላይ ያደረሰችው የአየር ድብደባ “የዓለም አቀፍ ህግን የጣሰ አይደለም” ብለዋል ሲል አል አረቢያ ዘገቧል።
የሩት ከመጪው የኔቶ የመሪዎች ጉባኤ ቀደም ብሎ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ጥቃቶቹ የተፈጸሙት “የቀጣናዊ ደህንነትን ከመጠበቅ እና የኒውክሌር መስፋፋትን ከመከላከል” አንፃር መሆኑን ጠቅሰዋል
ጋዜጣ ፓላስ


