“ሁለት-ረገጥ አካላት” ሲል አብን የጠራቸው የአማራ ክልል አመራር አካላት የሕዝብን ስቃይ እያባባሱ መሆኑን ጠቅሶ የማጥራት ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አሳሰበ። “የአማራ ክልል በማይመጥነው ቀውስ ውስጥ ነው” በማለት ትጥቅ ያነሱ አካላት ወደ ድርድር እንዲመጡ ጥሪ አቀረበ፣ ለሕዝብና ለመንግስትም የሰላም ጥሪ አሰምቷል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወቅታዊ የአማራ ክልል፣ ሀገራዊ እና ቀጠናዊ ጉዳዮችን መርምሮ የደረሰባቸውን ዋና ዋና መደምደሚያዎችና አቋሞች እንደሚከተለው ይገልጻል።
የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ
አብን በአማራ ክልል ውስጥ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር በህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ጉዳት ለተለያዩ አካላት ከማስገንዘብ ባሻገር ተጨባጭና ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል።
በክልሉ ውስጥ ያለው የጸጥታ ችግር ተባብሶ በመቀጠሉ፣ የግድያ፣ የእገታ እና የዘረፋ ወንጀሎች ተስፋፍተዋል። በግብታዊነትና በጠላት መንገድ መሪነት የተገባበት የትጥቅ እንቅስቃሴ ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት አስከትሏል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የመማር መብታቸው ተገፏል፤ ነጋዴዎች ንብረታቸውን በእገታና በቅሚያ አጥተዋል፤ በሕክምና እጥረት ሕሙማን ለሞት እንዲዳረጉ አድርጓል። የድንጋይ ዘመን የጎበዝ አለቃ አደረጃጀቶች በመበራከታቸው የቂም በቀል ግድያ፣ ዝርፊያና እገታ ወንጀሎች ጨምረዋል።
ለዚህም ራሳቸውን የሕዝብ ብቸኛ ወኪል አድርገው የሰየሙ ግለሰቦችና ቡድኖች፣ በአማራ ሕዝብ ስም የተደራጁ የዲያስፖራ ማህበራት፣ የጦርነት ኢኮኖሚ ተዋናዮች፣ በሙስናና ዝርፊያ የተሰማሩ በእየደረጃው ያሉ አመራሮች እና አንዳንድ ወታደራዊ ዲሲፕሊን የጎደላቸው የመከላከያ አባላት፣ የዝርፊያ፣ የማዋከብ፣ የኮንትሮባንድና የሰው ማዘዋወር ወንጀለኞች ግጭቱን የኢኮኖሚያቸው ቋሚ ምንጭ በማድረግ ለሕዝባችን መከራ ዋና ተጠያቂዎች ናቸው።
የአማራን ሕዝብ ለማጥፋትና ለማደናቀፍ አቅደው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች የትጥቅ እንቅስቃሴውን መልካም አጋጣሚ በማድረግ ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ እየተሳተፉ ነው። ዋናዎቹም ሻዕቢያና ህወሓት ሲሆኑ፣ ሕዝባችን የእነዚህ ጠላቶች የትብብር ድር መስሪያ ሆኗል። ይህም ሕዝቡን ለከፋ የደህንነት ስጋት፣ ለኢኮኖሚ ድቀት አልፎም ለህልውና አደጋ አጋልጧል።
በክልሉ መንግሥት ውስጥ የተሰገሰጉ ከ’ወያኔያዊ’ አስተሳሰብ ነፃ ያልወጡና የጎጥ ፖለቲካ ሰለባ የሆኑ አካላት ለችግሩ መባባስ ምክንያት ናቸው ብለን እናምናለን። በመሆኑም የክልሉ መንግሥት በውስጡ ያሉትን ሁለት-ረገጥ አካላት ለይቶ በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ አብን አጥብቆ ይጠይቃል።
የአማራን ሕዝብ አንድነት በማዳከምና ትግሉን ማዕከል አልባ በማድረግ የፖለቲካ ግቦችን ከስልታዊ መንገድ የማውጣት የጠላት ኃይሎች ዓላማ ከሞላ ጎደል ተሳክቷል። በአሁኑ ሰዓት የአማራ ፖለቲካ ወዳጅና ጠላት የማይለይበት፣ የሕዝብ ድምፅ የታፈነበትና የሰው ሕይወት ለሸፍጠኞች ግብዓት የተደረገበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በብዙሃኑ የሃገራችን ህዝቦችና ልሂቃን ዘንድ ሰፊ ተደማጭነት ያገኙ የነበሩት የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት በአሉታዊነት፣ በጥርጣሬና በስጋት እንዲታዩ ተደርጓል ። ይህ የሆነው የተሳሳተ የፖለቲካ አሰላለፍ በሚከተሉ ኃይሎች ጥፋት እንዲሁም በጠላት የተቀናጀ ፕሮፖጋንዳና ሴራ ነው ብለን እናምናለን።
አብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) የግጭትና የጦርነት ፖለቲካ በኢትዮጵያ ታሪክ ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ ፤ በጠላትነት ትርክት እርስ በርስ የተቆላለፉ ኃይሎች በትብብር የሚያጸኑት ፍትሕም ሆነ መንግሥት እንደማይኖር፤ እንዲሁም በሴራና በኃይል ሚዛን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ከወቅታዊ ጊዜያዊ ጥቅም ባለፈ ሊቀጥል አይችልም ብሎ ያምናል።
በልዩ ልዩ ምክንያቶች እንዲሁም የህዝባችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለማስመለስ በሚል ወደ ትጥቅ ትግል የገባችሁ ወንድምና እህቶቻችን የአሁኑ የትጥቅ እንቅስቃሴ ህዝባችን በእጅጉ የጎዳና ለታሪካዊ ጠላቶች ጥቃት በር እንደሚከፍት በመገንዘብ እንዲሁም አሁን ባለው አደገኛ ሁኔታ መቆየት የሕዝቡን ክብር እንደማይመጥን በመገንዘብ ወደ ድርድርና ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ በመምጣት ለአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ውለታ እንድትውሉለት አብን አጥብቆ ይጠይቃል።
የመፍትሔ አቅጣጫዎችና ጥሪዎች
አሁን በአማራ ሕዝብ ስም እየተካሄደ ያለው የትጥቅ እንቅስቃሴ የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች የማያሳካ፣ ይልቁንም የሻዕቢያና የወያኔ “ፅምዶነት” እንዲሰምርና ለታሪካዊ ጠላቶች በር የሚከፍት ነው። ስለዚህ፣ መፍትሔውም በቡድን ወገንተኝነት ያልተሸፈነ፣ በእውነት ላይ የተመሰረተና የህዝባችን ነባራዊ ሁኔታ መሰረት ያደረገና ችግሩን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል ብለን እናምናለን።
የክልሉ መንግስት፡- ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝቡን ለሰላምና ለልማት ለማነሳሳት የተደረጉ ጥረቶች የሚደነቁ ቢሆንም የክልሉ በየደረጃው ያለው አመራርና የፌዴራል መንግሥትአመራሮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ግጭቱ ሊቀለበስና ዘላቂ ሰላም ሊሰፍን አልቻለም። በተለይም በክልሉ መንግሥት ውስጥ የተሰገሰጉ ከ’ወያኔያዊ’ አስተሳሰብ ነፃ ያልወጡና የጎጥ ፖለቲካ ሰለባ የሆኑ አካላት ለችግሩ መባባስ ምክንያት ናቸው ብለን እናምናለን። በመሆኑም የክልሉ መንግሥት በውስጡ ያሉትን ሁለት-ረገጥ አካላት ለይቶ በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ አብን አጥብቆ ይጠይቃል።
የፌዴራል መንግስት፡- የፌዴራል መንግሥት የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት የማስጠበቅ ብሔራዊ ኃላፊነት አለበት። ስለሆነም ከሁለት ዓመት በላይ በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ መቀልበስ የሚያስችሉ ሕጋዊና ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን በአፋጣኝ እንዲሰጥ ጥሪ እናስተላልፋለን።
በተለያዩ ሀገራዊ የሰላም ማስፈን ተልዕኮዎች የሚሳተፉ የሀገራችን የቁርጥ ቀን ልጆች እና ህዝባችን ዋጋ የሚከፍለው በሁለት ቢላ በሚበሉ ሁለት-ረገጥ የፖለቲካና የጸጥታ አመራሮቹ እና ከውጭ ጠላት ጋር በሚተባበሩ አካላት ሴራ በመሆኑ መንግስት በእነዚህ ላይ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ አጥብቀን እንጠይቃለን።
ታጣቂ ቡድኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ የሚያበረታታ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጥርና የመልሶ ማቋቋም ስትራቴጅዎችን አስቀድሞ እንዲያዘጋጅ።
አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች የተቋረጡ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲቀጥሉና አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዲጀመሩ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ እናስተላልፋለን።
በክልሉ ውስጥ ያለው የጸጥታ ችግር ተባብሶ በመቀጠሉ፣ የግድያ፣ የእገታ እና የዘረፋ ወንጀሎች ተስፋፍተዋል። በግብታዊነትና በጠላት መንገድ መሪነት የተገባበት የትጥቅ እንቅስቃሴ ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት አስከትሏል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች የመማር መብታቸው ተገፏል፤ ነጋዴዎች ንብረታቸውን በእገታና በቅሚያ አጥተዋል፤ በሕክምና እጥረት ሕሙማን ለሞት እንዲዳረጉ አድርጓል። የድንጋይ ዘመን የጎበዝ አለቃ አደረጃጀቶች በመበራከታቸው የቂም በቀል ግድያ፣ ዝርፊያና እገታ ወንጀሎች ጨምረዋል።
ለታጠቁ ኃይሎች የቀረበ ጥሪ
በልዩ ልዩ ምክንያቶች እንዲሁም የህዝባችን መሰረታዊ ጥያቄዎች ለማስመለስ በሚል ወደ ትጥቅ ትግል የገባችሁ ወንድምና እህቶቻችን የአሁኑ የትጥቅ እንቅስቃሴ ህዝባችን በእጅጉ የጎዳና ለታሪካዊ ጠላቶች ጥቃት በር እንደሚከፍት በመገንዘብ እንዲሁም አሁን ባለው አደገኛ ሁኔታ መቆየት የሕዝቡን ክብር እንደማይመጥን በመገንዘብ ወደ ድርድርና ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ በመምጣት ለአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ውለታ እንድትውሉለት አብን አጥብቆ ይጠይቃል።
ለአማራ ሕዝብ የቀረበ ጥሪ
በስሙ የሚደረግን የፖለቲካ ንግድና የባንዳነት ተግባር በቃኝ ብሎ ዘላቂ ጥቅሞቹን የሚያከብርበትን መንገድ እንዲከተል። በጥቂት ልጆቹ የባንዳነት ተግባር ታሪኩንና ህልውናውን ሊያጠፋ ለሚችል እንቅስቃሴ መተባበር እንደሌለበት አውቆ፣ በመሠረታዊ ጥያቄዎቹ ላይ ትኩረት ካደረጉ ሐቀኛ የትግል እንቅስቃሴዎች ጎን ጸንቶ እንዲቆም ጥሪ እናስተላልፋለን።
ለመላው ኢትዮጵያውያን
ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ በርስ በርስ ግጭትና መጠፋፋት ውስጥ ትገኛለች። ዜጎች በየትኛውም ቦታ በሰላም መንቀሳቀስና መሥራት ካለመቻላቸው በተጨማሪ የእገታ፣ የዘፈቀደ የደቦ ፍርድ፣ የአስገድዶ መድፈርና የግድያ ወንጀሎች ሰለባ የመሆናቸው ጉዳይ የአደባባይ ሀቅ ነው። በመሆኑም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ይህንን ችግር ለማስቆም የተቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉና ለሰላም የሚደረገውን ጥሪ እንዲደግፉ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡
*****
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
መስከረም/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ

