ኬንያ በ2027 ከ1 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ ዜጎች አዳዲስ የስራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዷን አስታወቀች፡፡ ኢስት ሌይ ቮይስ የኬንያ የህዝብ ፖሊሲ ጥናት ተቋምና ምርምር ኢንስቲትዩት መረጃን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በሀገሪቱ በተጀመረው የኢኮኖሚክ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ንቅናቄ ሥር ለአንድ ሚሊየን 788 ሺህ 881 በቀጥታና በተዘዋዋሪ ለዜጎች አዳዲስ የስራ ዕድል ይፈጠራል፡፡
407 ሺህ 732 ያህሉ የሥራ ዕድል በቀጥታ ይፈጠራል ሲሆን፤ አንድ ሚሊየን 381 ሺህ 149ኙ ደግሞ በተዘዋዋሪ የስራ ዕድል የሚፈጠርላቸው መሆናቸውን ተመላክቷል፡፡
የሥራ ዕድሉ በግብርና፣ በመሰረተ ልማት፣ በትምህርት፣ በጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ዘርፎች የሚፈጠር መሆኑም ተነግሯል።
የመሰረተ ልማት ዘርፍ 697 ሺህ 809 የሥራ ዕድል የሚፈጠርበት እና ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፤ በትራንስፖርቱ ዝርፍም 309 ሺህ 538 የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተጠቅሷል፡፡
በተጨማሪም የፋይናንስና አምራች ዘርፉ ከአምስት መቶ ሺህ በላይ የስራ ዕድል እንደሚፈጠር የተጠቀሰ ሲሆን፤ ይህም የሀገሪቱን ዕድገት በ7 ነጥብ 3 በመቶ ከፍ ያደርገዋል ተብሏል፡፡

